ስንዱ እንቁዋን ንቃ፣
 የሰው መዳብ ያምራል ብላ፡
         በ፵፩ ዓመተ ምህረት ከሰዳቢዎቿ ተደባልቃ።
 ማለቂያ ከሌላቸው ሁከተኞች ተራ፥
 ከጋለሞቶች ተደምራ።
 በ፷፯ ቢደግሱላት፡
 የጋለሞቶች ቁንጮ ሊያደርጓት።
  በቀኑ፥
         የመበለትነት ማቅ ለበሰችበት።
 ስንዱ አልቀረላት፡
 ጋለሞቶች እንደገና ሸነገሏት።
 በአዲሱ ዘመን አቅራቢያ፡
 ወንበራችን እነሆ አሏት።

 ስንዱ ስሟ በወንበሩ ተጠራ፡
 ጋለሞቶችም አሉ፥
         ስንዱ ገባች ከኛ ተራ።
 ከጋለሞቶች መንደር፡
 ባሏ ከማይደርስበት ሠፈር።

 ስንዱ፥
 አንቺ ሙሽራ፡
 የተቆለፍሽ አዝመራ።
 መዓዛሽ ከሊባኖስ የተመረጠ፡
 ከሽቱ ሁሉ የበለጠ።
 ቡቃያሽ ገነት የሮማን ፍልቃቂ፡
 አንቺ የህይወት ወንዝ፡
         ከታተመ ምንጭ የምትፈልቂ።
 ከጋለሞታ ሰፈር በገባሽ ማግስት፡
 ውድሽ ከቤትሽ እንዳልመጣ፡
 ዝማሬሽ ተቀባይ እንዳጣ፡
 እጣንሽ ወደላይ እንዳልወጣ፡
 መርዶው የእንግልትሽ የኃዘኑ፡
 እነሆ ይድረስሽ በስልሳ ዘመኑ።
 ስንዱ ተነሽ፡
 እረኛሽን ፈልጊው ከበረሃው።
 ተናገሪው፡
 የሰሜን ነፋስ ሆይ ተነስ፣
         የደቡብም ነፋስ ና በይው።
 ውድሽ ቀናተኛ ነውና፡
 መዓዛሽን ይወዳልና፡
 የጋለሞታውን መንደር ተይው።

 ስንዱ፥
 ማር ከከንፈሮችሽ እንዲንጠባጠብ እንደገና፡
 እጣኑ ከኮረብታሽ ወደሰማይ እንዲያቀና፡
 ተራራሽ ካጋለሞቶች ሜዳ እንዲልቅ፡
 ከጉድጓድሽ የህይወት ውኃ እንዲፈልቅ፡
 ወድሽ ወደ ገነትሽ እንዲመጣ፡
 እግርሽ ከጋለሞቶች ማህበር ይውጣ።ኢትዮጵያና የዓለም እምነቶች ማህበር።


 HOME