ከጥቂት ዓመታት በፊት ስለተክሎችና ስለ ዝናም እውቀት ለመገብየት መጻሕፍትና ድርሰቶችን ሳገላብጥ "የዳመና አርበኞች" የሚባሉትን የዳመና አሳዳጆች ጩኸት አየሁ። የዳመና አርበኞች በተለይ ስለ ዳመና ስርቆት የሚጽፉት አስገረመኝ። ዳመና እንዴት ሊሰረቅ ይችላል? - እነዚህ የሚቃጁ ሰዎች   ሳይሆኑ አይቀሩም ብየ ችላ አልኳቸው፤ ቢሆንም በጽሁፋቸው ላይ በማስረጃነት የጠቀሷቸውን መጻሕፍት ፈልጌ አነበብኩ። በተለይም "መላእክት የማይጫወቱት በገናበሚል አርእስት የተጻፈውን መጽሐፍ ሳነብ ልቤ ተጨነቀ።  መላእክት የማይጫወቱት በገና የሚባለው መጽሐፍ ጉልበት ያላቸው አገሮች  ለሆድ ወይም "ለብሔራዊ ጥቅም" ሲሉ የምድርን የአየር ጸጋ እንዴት እንደሚያውኩት በማስረጃ አስደግፎ ያስረዳል። ጉልበት ያላቸው አገሮች ለሌሎች የሚደግሡትን አስፈሪ ድግሥ መጽሐፉ በዝርዝር ይተነትናል።

በተለይም
 በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት የአማሪካ ፕሬዚዳንት ሊንዳ ጆንሰን የሳይንስ አማካሪ የነበሩትና በተለይ የአማሪካ የስለላ ድርጅት የሚኮራባቸው ዶክተር ጎርዶን ማክዶናልድ የሚባሉት ጂኦ ፊዚዚስት ምእራባውያን ሊጠቀሙበት ይገባል ብለው የነደፉት የአየር አያያዝ ትልም ወይም በምእራባውያን ቋንቛ የአየር ንብረት ጂኦስትራቴጂ  እጅግ በጣም የሚያስደነግጥ መሆኑን አየሁ። ዶክተር ጎርዶን ማክዶናልድ ይህን ህልማቸውን "ወደ ሁለት ሺህ አሥራ ስምንት ዓመተ ምህረት"   በተባለው  እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በአስራ ዘጠኝ መቶ ስልሳ ስምንት ዓመተ ምህረት በተጻፈው የአማሪካ ዋና ዋና ሳይቲስቶች  "የራእይ" መጽሐፍና "አየርን መበጥበጥ" በሚለው መጽሐፋቸው ላይ አስፍረውታል። እንዲህ ብለውም ጻፉ፥ ከአሁን በኋላ ጠላቶቻችን የጦር መሣሪያ አንስተን መዋጋት የለብንም። ይልቁንስ ወደፊት ጠላቶቻችን ሊሆኑ የሚችሉ አገሮች እነማን ናቸው ብለን በጥናት ካወቅን በኋላ የእነዚህ ወደፊት ጠላቶቻችን ሊሆኑ የሚችሉ አገሮች ሰዎች ሳያውቁ የአየር ንብረታቸውን ከርቀት የአየርን ንብረት በሚቀይር የቴክኖሎጂ መሣሪያ እያዛባን በተደጋጋሚ ለድርቅ እናጋልጣቸዋለን እነዚህ ህብረተሰቦች በድርቅና በረሃብ ከተንበረከኩ በኋላ እኛ የምናቀርብላቸውን አማራጭ ያለማቅማማት እንዲቀበሉ ማድረግ እንችላለን። አንድ ጊዜ በድርቅና በረሃብ ከተጎዱ በኋላ እግረኞችን ልከን የኛን ፍላጎት መቀበላቸውን ማረጋገጥም እንችላለን። 

መላእክት የማይጫወቱት በገና በሚባለው መጽሐፍና በሌሎችም ስለ አየር መዛባት በሚተርኩ መጻሕፍት እንደሰፈረው የዶክተር ጎርዶን ማክዶናልድን ራእይ እውን ለማድረግ በፈርንጆች አቆጣጠር ከስልሳወቹ መጨረሻ ጀምሮ በዓለም ላይ ብዙ አየርን የማዛባት የሳይንስ ሙከራወች ተደርገዋል። በሰማይ መሬትን የከበበውን አየር አዮኖስፌሪክ ሺፋን የኤሌክትሮ ማግኔት ሞገድ አንጸባራቂነት ባህርይ በመጠቀም በዓለም ላይ ያለ የተፈለገውን ቦታ የአየር ጠባይ በቀላሉ የሚያውከው፣ ካስፈለገም የአንድን ሰፈር ወይም ሃገር ህብረተሰብ በሙሉ የአእምሮ በሺተኛ ማድረግ የሚችለው ሃርፕ   የተባለው በአላስካ ተተክሎ የሚገኘው አየር አዋኪ መሣሪያ የተገነባው እንዲሁ የዶክተር ጎርዶን ማክዶናልድ ራእይ እውን ይሆን ዘንድ እንደሆነ መጽሐፎቹ ያወሳሉ።

ታዲያ እነዚህን መጻሕፍቶች ሳነብ በአገሬ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቼ በድርቅ ምክንያት በረሃብ መርገፋቸውን አስታወስኩ። ለቅጽበትም ያህል ይህ በአየር ንብረት ላይ የሚፈጸም ግፍ በአገሬ ላይ ተፈጽሞ ይሆን ወይ? ብየ አሰብኩ። የአየር ብጥበጣ ሙከራ ይደረጉ የነበሩባቸው አመታት ከኢትዮጵያ የድርቅ አመታት ጋር የተቀራረቡ መሆናቸውንም አጤንኩ። የኢትዮጵያውያንን በረሃብ መንበርከክ አይተው "ለበጎ" አድራጎት በሚል ርዕስ የሚመጡ ኃይማኖታችሁን ተውና የኛን ተቀበሉ የሚሉ ድርጅቶችንና ፓስተሮችንም አስታወስኩ። እነዚህ እንግዶች ከብዙ የሚቆራርጥ እምነታቸውንና ፍልስፍናቸውን በኢትዮጵያውያን መካከል ሲዘሩም ትዝ አለኝ። እነዚህ ድርጅቶችና ፓስተሮች ዶክተር ጎርዶን ማክዶናልድ ያወሷቸው እግረኞች ናቸውን? ብየም አሰብኩ። ትንሽ ቆይቼ ግን እግዚአብሔር ከፈጠረው ከሰው ልጅ ይህን ያህል ክፋት ሊመጣ አይችልም፤ የክፋት ሃሳብ ቢፈልቅም ብዙ ሰዎች ተባብረው ክፋትን እውን ሊያደርጉ አይነሱምና ምእራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ይህን የመሰለ ጥቃት ሊፈጽሙ አይችሉም ብየ እንዲያውም እራሴን እንደዚህ በማሰቤ ወቀስኩት። እንደገናም ኢትዮጵያ ለማንም ጠላትነት የሚያበቃት ሥራና አቅም  የላትምና የማታውቃቸው ጠላቶች አይኖሯትም ብየ እራሴን አጽናናሁት።   

ሆኖም ግን አሁን በግብጽ የምናየው ትርምስ ብዙ ነገርን ገለጠ። ሰሞኑን በግብጽ ያለው ሁኔታ ከግብጽ መሪዎች ይልቅ አንዳንድ ሌሎች አገሮችን እጅግ በጣም ስላስደነገጣቸው የግብጽ አስተዳደር ቢቀየር የዓለም ሚዛኗ ይዛባል እያሉ የምእራብ መንግሥታትን ሲማጸኑ አየን።  በዚህ በድንገተኛ ትርምስ ውስጥ ብዙ፣ እጅግ ብዙ ትምህርቶችን ተማርን።  በፈረንጅ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብቶ ከመማር፣ በምእራባውያን የተጻፉ መጻሕፍትንም ከማንበብ፣ በዓለም አገሮች ግንኙነቶች እውቀት የተራቀቅን ነን የሚሉ ሰዎችንም ከማዳመጥ ሁሉ የበለጠ ብዙ ትምህርትን ገበየን። በግብጽ በጨለማው ውስጥ የተቀጣጠለው የእሳት ነበልባል ብልጭታ በጨለማ ተጋርደው በኢትዮጵያ ላይ የተጫኑትን ቀንበሮችን አሳየን።

እነሆ በጋዜጣና በልዩ ልዩ የመገናኛ ማእከሎች እንደምናነበውና እንደምንሰማው የግብጽ መሪ ሙባረክ ለአይሁድ መንግሥት መከታ ሆነው መቆየታቸውን ተማርን። የአይሁድና የምእራብ መንግሥታትም የግብጽ መሪ መከታ ሆነው ስለመቆየታቸውም ተማርን። የካምፕ ዴቪድ ውል በሚባለው የተደረገው ስምምነት የግብጽ መንግሥት በአይሁድ መንግሥት ላይ፣ የአይሁድ መንግሥት ደግሞ በግብጽ መንግሥት ላይ ጦርነት እንዳይከፍቱ ነው ሲባል ሰማን ይህ አደባባይ ላይ የወጣው ገጽታ እንደሆነም አየን። የአይሁድ መንግሥትና ምእራባውያን በአንድ በኩል፤ የግብጽ መሪዎች በሌላ በኩል ያደረጉት አደባባይ ያልወጣውን ሚስጢር ግን ብዙ ጋዜጦች በተዘዋዋሪ መንገድ በጽሑፍ አስፍረውት ሰሞኑን አነበብን። አንዳንዶቹ ጸሐፊዎች የምእራባውያን መንግሥታት የቅርብ የትልም አማካሪዎች ናቸው። እንዲህም ይላሉ፥ የግብጽ መንግሥት የአይሁድ መንግሥት ማገር ነው። የግብጽ መንግሥት ከሌለ የኢራንን እርምጃ ማን ይገታልናል? እያሉ ሲጨነቁ ሰማን። ለግብጽም ለራሷ ቢሆን ከዚህ ከግብጽ መንግሥት ጋር ባለ ውለታ አይደለም እንዴ የግብጽን ጥቅም ያስጠበቅነው? አሁን ግብጽ ከኛ ጋር ውሉን የጠበቀ መንግሥት ካላመጣች ኢትዮጵያን በድህነትና ያለባህር በር ማን ሊያቆይላት ነው እያሉ የግብጽን "አመጸኞች" ሲያስጠነቅቁ አየን።

ማንም ዝቅተኛ የግንዛቤ ችሎታ ያለው ኢትዮጵያዊም እንኳን ቢሆን ጽሁፎቹን በማየት በኢትዮጵያ ላይ ከሠላሳ ዓመታት በላይ ተጭኖ የቆየውን የግብጽ፣ የአይሁድና፣ የምእራባውያንን የጣምራ ቀንበር ግዝፈትና ክብደት ማየት ይችላል።  በግብጽ ከሰላሳ ዓመታት በላይ ሲገነባ የኖረው የጥፋት መሣሪያ፣ ታንኮቹ፣ ሚሳይሎቹ፣ ተዋጊ አውሮፕላኖቹ ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ እንዲውሉ ታስቦ መሆኑም እነሆ ግልጽ ሆነ።  እንደምናየው የግብጽ መንግሥት፣ የአይሁድ መንግሥትና ምእራባውያን ኤርትራን ከኢትዮጵያ ያስገነጠሉት ኢትዮጵያን በድህነት እንድትማቅቅ ለማድረግና በተጨማሪም፣ በባቢሎን አገላለጽ፥ "ኢትዮጵያን ከጂኦ ስትራቴጂ ጨዋታ ውጭ ለማድረግ" ነበር። በኢትዮጵያ ውስጥም በተለያየ ቦታ ኢትዮጵያውያንን በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያስነሱትም ሆነ የሚከፋፍሉት ስለ መብት አስበው ሳይሆን ኢትዮጵያን ድሃ ስለማድረግ ነበር። አሁን ይህ የሰሞኑ እሳት የገለጠውን ሚስጢር ሳይ በእርግጥ ብዙ ሰዎች ተስማምተው ክፋትን ለማከናወን ሊነሱ እንደሚችሉ ተገነዘብኩ። ሳትበድላቸው  ኢትዮጵያን የደኸየችና የባህር በር የሌላት አድረግን ማቆየት አለብን የሚሉትን ምእራባውያንን ሳይ ድርቆቿን እነሱ አልደገሱትም ብየ ከዚህ ቀደም እራሴን የወቀስኩት ትክክል አይደለም ብየ እንደገና እራሴን ወቀስኩት። ደግሞስ የአፍሪቃ አገሮች ድሮ ኢትዮጵያን እንደ-የነጻነት የተስፋ ምልክት አድርገው ይመለከቷት አልነበረምን? የአፍሪቃ አገሮች ኃይማኖታቸው የኢትዮጵያ ኃይማኖት ቢሆን ኖሮ አንድ ሆነው የሚመክቱ፣ ነጻነታቸውንም የሚያስከብሩ አይሆኑም ነበርን? ይህን የኢትዮጵያን ታሪኳንና አፍሪቃን ማገናኘት የሚችለውን እምነቷን ሳስብ ምእራባውያን ወደፊት ጠላታችን ልትሆን የምትችል አገር ናት ብለው ለምን ሊነሳሱ እንደሚችሉ ገመትኩ። በተራራማ ተፈጥሮዋ ምክንያት ዝናም በቀላሉ የምትማርከው ኢትዮጵያ አሁን የደረቁ  ወንዞቿን ብታዩ   ሰፊ የአለት አልጋ ያላቸውና ቁጥቋጦ የጎደላቸው በመሆኑ አደራረቃቸው ድንገተኛ መሆኑን መገመት ትችላላችሁ። የማውቀን አምቄ ማስቀመጥ መልካም አይደለምና እነሆ እናንተም አወቃችሁ።

እንግዲህ የችግሩ ሁሉ መንስኤ እነሆ ተገለጠ። እግዚአብሔር በኢሳያስ አንደበት እንደተናገረው፣ በሕዝቤ ላይ ለጥቂት ጊዜ ተቆጥቸ እርስቴን ለባቢሎን አሳልፌ ብሰጥ ባቢሎን ያለርኅራሄ ከባድ ቀንበርን ጣለችባቸው ብሏልና፥ አድምጡ። የባቢሎንን ቀንበር የሚያነሳ ኃያሉ እግዚአብሔር ብቻ ነው። የችግሩን ምንጭና ችግሩን የሚፈታውን ኃያሉን የኢትዮጵያ አምላክ በመተው የጉልቻ መቀያየር ላይ ማተኮር ምን ትርፍ አለው? በማያደርስ መንገድ መራመድ ቀርቶ ቢሮጡ ሊደርሱ ይችላሉንበኢትዮጵያ መንግሥታት ቢቀያየሩ በመንበሩ ላይ እግዚአብሔር እስከሌለ ድርስ ምንም ጊዜ  ቢሆን ከባቢሎንና ከግብጽ ቀንበር ኢትዮጵያ ልትላቀቅ አትችልም። ባቢሎን እና ግብጽ ደግሞ ስትራቴጂ ብለው የያዙት ኢትዮጵያን ድሃ አድርጎ ማስቀረትን እንድሆነ እነሱው እራሳቸው ሲናዘዙ አያችሁ።  እራስን ሳይቀይሩ በየአደባባዩና በየከተማው የሚደረግ ሰልፍ ሁሉ የባቢሎንን ቀንበር ለማገላበጥ ካልሆነ በቀር ለኢትዮጵያ ነጻነትን አያቀዳጅም።

ኢትዮጵያውያን ሆይ፥ እስከዛሬ ድረስ ግብጽ ኢትዮጵያን ድሃ ለማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ብዙ የውስጥ ብጥብጥ የምትፈጥርና ኢትዮጵያ በልማት እንዳትራመድም የውጭ ወጥመድን የምታጠምድ አገር እንደሆነች ነበር ብዙዎቻችን የምናስበው። ያላወቅነው ነገር ግን እንደዚህ የምታደርገው ግብጽ ሳትሆን የግብጽ መንግሥት ሥጋት እንዳያገኘው፣ ወይም በሥጋት ምክንያት ውሉን እንዲጠብቅ ሲሉ ኢትዮጵያን በመበታተንና በረሃብ ቅጣት ወደ መቃብር ያወረዷት የአይሁድ መንግሥትና ምእራባውያን መሆናቸውን ነው። ከላይ እንደምናየው በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጡት ባላጋራዎቿ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድም ሳይቀር ቢሰለፍ ሊቋቋማቸው የማይችል ኃያላን ናቸው። ኢትዮጵያ ከላይዋ ላይ የወደቀባትን ቀንበር ልታስወግድ የምትችለው በእግዚአብሔር ኃይል ብቻ መሆኑን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊያውቅ ይገባል። ኢትዮጵያዊው አማራጭም የለውም። በቅዱሳን መጽሐፍ የተጻፈችው፣ ኃያላን መንግሥታት፣ ግብጽና ባቢሎንም በዙሪያዋ የሚያስጨንቋት አገር በእንግሊዝና በምእራባውያን አነሳሺነት በተባበሩት መንግሥታት የዛሬ ስልሳ አመት የተመሠረተችው እግዚአብሔርን ማገልገል ቀርቶ ፈጣሪነቱን የማትቀበለው የአይሁድ መንግሥት አይደለችም። ግብጽና ባቢሎን፣ የዓለምም ኃይለኞች፣ በባቢሎን እና በግብጽ አበረታችነት ከጽዮን የተለዩት ኢትዮጵያውያንም ሳይቀር በጠላትነት የከበቧት አገር እግዚአብሔር መከታዋ የሆነችው ኢትዮጵያ መሆኗን አትዘንጉ። እጃችሁንም ወደ  ንጉሧ ወደ እግዚአብሔር ዘርጉ። እግዚአብሔር በኢትዮጵያ የመሠረተውንም የዳዊት ስርወ መንግሥት እንዳፈረሳችሁ ከንስሐ ጋር መልሱ።  ለኢትዮጵያ አርነት ከዚህ ውጭ ሌላ መንገድ የለምና።                
 

የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይመስገን።

ሙሉጌታ
ስንዱ፥ ዳመናዎችሽ የት ሄዱ?

 HOME