በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አኃዱ አምላክ አሜን

በምድር ላይ ተጽፈው ከምናያቸው ከታሪክ፣ ከፍልስፍና፣ ከኪነጥበብ፣ ከሳይንስ፣ ከኃይማኖትና ከሌሎችም መጻሕፍት አንድም መጽሐፍ ቅዱስን የሚያህል አይገኝም። መጽሐፍ ቅዱስ ህይወት ነው፥ ለሚያምኑ የህይወት ውኃ ይፈልቅበታል። መጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ ነው፥ ጸጋው ያላቸው ይጠልቁበታል፤ ጸጋውን ያላገኘ ጥልቀቱን ሊያውቅ አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ  ምግብ ነው፣ የተራቡት ይገነቡበታል፤ ያልተራቡት ያኘኩ ይመስላቸዋል እንጂ አይመገቡትም። መጽሐፍ ቅዱስ በቀትር ከጥላ ስር እንደሚፈልቅ የማያቋርጥ ምንጭ ነው፥ የተጠሙት ይረኩበታል። አይሁዶች እናውቀዋለን ይላሉ፣ ክርስቲያኖች ነን የሚሉም እንዲሁ፤ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥልቀት ግን እንደ ኢትዮጵያ ተዋህዶ ቅዱሳን በጥልቀት የጎበኘ ማንም የለም።

መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ይጻፍ እንጂ የመልእክቱ ባለቤት እግዚአብሔር በመሆኑ የሚስጢሩ ጥልቀት ከሰውና ከመላእክት ግንዛቤ በላይ ነው። እግዚአብሔር ካልፈቀደ በቀር ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ሊተረጉም አይቻለውም። ሰው በገዛ ፈቃዱ፣ ሄርሜኑቲክስ በሚባለው በምእራባውያን የፍልስፍና ዘይቤም ቢሆን፥ መጽሐፍ ቅዱስን ቢተረጉም ይሰናከልበታል። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደጻፈው  በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።[፩] በኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸጋውን በሰጣቸው ቅዱሳን በአንድምታ ይተረጎማል። አንድምታ ከአንድ ሰምና ከአንድ ወርቅ የጠለቀ ቅኔ ነው። ሰምና ወርቅ አንዳንድ ጊዜ መሃል የቆመ፣ ሌላ ጊዜ የተለየ አንድ ምሱል (ሰም) ገጽታ እና አንድ ጥሉቅ (ወርቅ) ገጽታ ሲኖረው፤ አንድምታ ግን ብዙ ልዩ ምሱላዊ ገጽታወች በምሳሌነት፣  አንድ ወይም ብዙ መንፈሳዊ ትርጉሞችን ደግሞ በወርቅነት ይይዛል። ለምሳሌ አብርሃም ልጁን ይስሃቅን አስሮ በመሠዊያው ላይ ሲያጋድመው፣[፪] ይስሃቅ ምሱላዊ ገጽታ ሆኖ የምሳሌው መንፈሳዊ ትርጉም ወልድ ሲሆን፥ አብርሃም ምሱላዊ ገጽታ ሆኖ መንፈሳዊ ምሳሌነቱ ለአብ ነው። የእግዚአብሔር መልአክም አብርሃምን በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፥ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለኔ አልከለከልህምና፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን አውቄያለሁ አለው። አብርሃምም አይኑን አነሣ፥ በኋላውም አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በእፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፡ አብርሃምም ሄደ በጉንም ወሰደው፥ በልጁም ፋንታ መስዋእት አድርጎ ሠዋው።[፫)  በጉ ምሱላዊ ገጽታ ሆኖ መንፈሳዊ ምሳሌነቱ ለክርስቶስ ሲሆን፤ እፀ ሳቤቅ ምሱላዊ ገጽታ ሆኖ ምሳሌነቱ ለመስቀል ነው። ምሱላዊ ገጽታ ዕፀ ሳቤቅ እንደገናም የክርስቶስን ምሳሌ በጉን ስለተሸከመ መንፈሳዊ ምሳሌነቱ ለቅድስት ድንግል ማርያም ነው። እንደገናም ሳቤቅ ይቅርታ ማለት ሲሆን፥ በክርስቶስ መስቀል ላይ መዋል የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ይቅርታን አግኝቷልና፣ መልሶም በእጸ ሳቤቅ ላይ በተሰቀለው በግ ምክንያት በምሱላዊ ገጽታ የዳነው ይስሃቅ በመንፈሳዊ ገጽታ በመስቀል የዳነው የሰው ልጅ ምሳሌ ነው። እነሆ የእግዚአብሔር ቅኔ ጥልቀቱ መለኪያ እንኳን የለውም። እፀ ሳቤቅ ትርጉሙ ይቅርታ ማለት ስለሆነ በጉ በሱ እንዲሰቀል ተመረጠ ወይንስ እፀ ሳቤቅ ወደፊት ስለሚመጣው መስቀል ወይም ወደፊት ስለምትወለደው ድንግል ማርያም ተፈጥሮ እፀ ሳቤቅ ተባለ? ካይፋ ማለት አለት፣ ፊሊጶስ ማለት ፈረስ-ወዳጅ፣ ማቴዎስ ማለት የእግዚአብሔር ስጦታ፣ ዳዊት ማለት ተወዳጅ መሆኑን ስናይ፡ አፈጣጠራቸው  ስለቀጠሮ፣ የስማቸው አወጣጥም ለቀጠሮው የተዘጋጀ እንደሆነ እናያለን። ስለዚህ እፀ ሳቤቅ ለመስቀልና ለድንግል ማርያም ተፈጠረ እንጂ፤ ስሙ እፀ ሳቤቅ ስለሆነ ለበጉ መስቀያነት አልተመረጠም። የመጽሐፍ ቅዱስ የምሳሌ ቅኔ ሰሞቹና ወርቆቹ  በጊዜ ሊለያዩ ይችላሉ። ለምሳሌ በእፀ ሳቤቅ የተሰቀለው ምሱላዊ ገጽታ በግ እና በክርስቶስ ስቅለት መካከል የአንድ ሺህ ስምንት መቶ ሰማኒያ አመት አካባቢ የጊዜ ልዩነት አለ። ይህ የሚያሳየን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ቀጠሮ መሆኑን ነው።  

ቀጠሮ

እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ፈጠረ።  በገነትም አኖረው። ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምን እና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፥ ከርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና ብሎ አዘዘው። እግዚአብሔር አምላክም አዳም ብቻውን ሊሆን መልካም አይደለም ብሎ በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፣ ከአዳም ጎንም አጥንት አውጥቶ ጎኑን በሥጋ ሞላው። እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት። ሚስት ትሆነው ዘንድ ወደ አዳምም አመጣት። በገነትም እባብ መጥቶ ይህችን ሴት አነጋገራት። እባብ ተንኮለኛ ነበርና ከገነት መካከል ካለው ዛፍ ብትበሉ አትሞቱም፤  እንደ እግዚአብሔር ክፉና ደጉን የምታውቁ ትሆናላችሁ እንጂ ብሎ ሴቷን አማከራት፥ አሳመናትም። ሴቷም ካዛፏ ፍሬ ወስዳ በላች፥ ለባሏም ሰጠችው። አዳምም ከእርሷ ጋር ሆኖ በላ። እግዚአብሔር ከዚህ ዛፍ ፍሬ ከበላችሁ ሞትን ትሞታላችሁ ብሏቸው ነበርና፥ አዳምና ሴቷ ሄዋን ከገነት ተባረሩ፣ የሞት ቀንበርም ተጫነባቸው። እግዚአብሔር አምላክ እባብን ከአራዊት ሁሉ ተለይተህ የተረገምህ ትሆናለህ፣ በሆድህም ትሄዳለህ፣ አፈርንም በህይወት ዘመንህ ሁሉ ትበላለህ አለው። በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፥ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ አለው። [፬]  

የእግዚአብሔር ቅኔ የጠለቀ ሚስጢር ነውና ከላይ እንደምናየው በዚህ በእርግማን ውስጥ የምህረትን ምሳሌ አሰናዳ። ከሴቷ የእባቡን ዘር ዲያቢሎስን የሚቀጠቅጥ ክርስቶስ እንደሚወለድ እግዚአብሔር ቅኔ ተቀኜ።  በዚህም አዳም የክርስቶስ፥ ሄዋን ደግሞ የድንግል ማርያም ምሳሌ ሆነች። እግዚአብሔር አምላክ ከአዳም አጥንትን ነስቶ ሄዋንን ፈጠረ፥ እሷም በእባብ አማካሪነት ያመጣችውን ምግብ ሰው በልቶ ሞተ፤ እግዚአብሔር አምላክ ከድንግል ማርያም ስጋን ነስቶ፡ ቃል አምላክ ሥጋ ሆነ። ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ተወለደ። በመስቀል ላይ ተሰቀለ፣ ሞተ፣ ከሙታንም ተለይቶ ተነሳ፣ ወደ ሰማይም አርገ፡ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ። ሰው መንግሥተ ሰማያት ይገባ ዘንድ አዲስ ሕግና ሥርአት መንገድ ሠራ። መንገድም እራሱ ሆነ። በሱ ያመነ፣ የተጠመቀ፣ ሥጋውን የበላ፣ ደሙን  የጠጣ፣ የተራበውን የመገበ፣ የተጠማውን ያጠጣ፣ የታረዘውን ያለበሰ፣ የታመመውን የጠየቀ፣ የታሠረውን የጎበኘ በዚህ መንገድ ሄደ። እግዚአብሔር አምላክ ከድንግል ማርያም ተወለደ። ከሞት ህይወትን ሠራ።  ሞቷን ወስዶ ህይወቱን ሰጣት። በሄዋን በኩል ሰው ሞተ፣ በድንግል ማርያም በኩል ሰው ዳነ። እግዚአብሔር አምላክ የሴቷ ዘር የእባቡን ዘር አናት ይቀጠቅጣል፥ እባብም የሴቷን ዘር ሰኮና ያሳድዳል፣ እባብም፣ በሆዱ ይኖራል ብሏልና፥ በእግዚአብሔር አምላክ  ቀጠሮ፥ ክርስቶስ የሴቷ ዘር እባቡን ዲያቢሎስን ቀጠቀጠ፣  በሆዱ የሚሄደው ወይም ስለሆዱ የሚኖረው ዲያቢሎስም ብጽእት ድንግል ማርያምና ወገኖቿን ሲያሳድድ አሁን እናያለን። እነሆ በቀጠሮው የእባቡ ወገኖች በብጽእት ድንግል ማርያምና በወገኖቿ ላይ ጦርነት ከፍተዋል።

በዚሁ የኦሪት ዘፍጥረት ምሳሌ ሌላም ቅኔ ሰፍሯል። ሴቷ ሄዋን ከዛፉ ፍሬ እንድትበላ እባብ የመከራት ክፉና ደጉን የሚያስታውቀው ዛፍ የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ጠቅሶ ነው። እንደገናም በኦሪት ዘፍጥረት አቤልና የስሙ ትርጉም ወሳጅ የሆነው ቃኤል ለእግዚአብሔር መሥዋእትን አቀረቡ። እግዚአብሔር አምላክም የአቤልን መሥዋእት ተቀበለ፣ የቃኤልን ግን አልተቀበለም። በዚህ ምክንያት ባደረበት ቅናት ቃኤል ተነስቶ ወንድሙን አቤልን ገደለው። ቃኤልም የተረገመ ሆነ። ይህ ቅኔ እናምናለን የሚሉ ሁሉ አማኞች አለመሆናቸውን በምሳሌ ይነግረናል። የምሳሌዎቹ ትምህርት የድንግል ማርያምና የወገኖቿ ጠላቶች የሆኑት የዲያቢሎስ ወገኖች እመቤታችን ድንግል ማርያምንና ወገኖቿን የሚያሳድዱት እንደቀደመው እባብ የእግዚአብሔርን ቃል በመጥቀስ ነው። መልሶም ሌላ ቅኔ በዚሁ ምሳሌ ውስጥ ይገኛል። እባብ ወደ ገነት መጣ እንጂ፤ ሴቷ ሄዋን ወደ እባቡ አልሄደችም። እባቡም ወዳጅ መስሎ በገነት ውስጥ ተገኜ እንጂ በጠላትነት አልቀረበም። እነሆ የእባቡንና የዲያቢሎስን ወገኖች በምሳሌው ምልክት እንድንለይ እግዚአብሔር በቅኔው ውስጥ ሌላ ቅኔ ተቀኜልን።

እንደምናየው መጽሐፍ ቅዱስ ጥልቀቱ ሊለካ የማይችል የምሳሌ ቅኔ ውቅያኖስ ነው። የምሳሌውን መንፈሳዊ ትርጉም ወስደን ምሳሌውን ወደ ጎን እናድርግ ማለት አይቻልም። ከላይ እንዳየነው ጥልቁ የእግዚአብሔር ቅኔ መንፈሳዊ ትርጉም መልሶ ምሳሌውን በቅኔ ይቀኜዋልና። ለምሳሌ እግዚአብሔር አምላክ ሙሴን በኮሬብ ተራራ ይህ ቦታ የተቀደሰ ነውና ጫማህን አውልቅ ያለበትን ቅኔ መንፈሳዊ ትርጉሙ ኃጢአትህን በንስሃ አውልቀህ ጣል ማለት ነው ብንልና፤ መንፈሳዊ ትርጉሙ ሌላ ነው ብለን ምሳሌውን ልንጥስ ቢቃጣን፥ የሄዋንን ጥፋት ደገምን እንደማለት ነው፥ የእግዚአብሔር ቅኔ ምሱላዊ ገጽታውም ሆነ መንፈሳዊ ትርጉሙ ሁሉም ጥልቅ ቁምነገር አላቸውና። 

መጽሐፍ ቅዱስ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ የዮሐንስ ራእይ ድረስ በተለያዩ ምሳሌዎች ስለሁለት ሠፈሮች ይቀኛል። አንዱ የቅዱሳን ሠፈር ሲሆን ሌላው የዲያቢሎስ ሠፈር ነው። የቅዱሳን ሠፈር ወደ ሕይወት መንገድ ወደ ክርስቶስ ያደርሳል፣ የዲያቢሎስ ሠፈር ወደ ሞት ያመራል። ስለነዚህ ስለሁለቱ ሠፈሮች  መጽሐፍ ቅዱስ፡ ብዙ፥ እጅግ በጣም ብዙና ጥልቅ ቅኔዎችን ይቀኛል። የቅዱሳን ሠፈር ቅኔዎች የክርስቶስና የክርስቶስ ከተማ፥ የብጽእት ቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌዎች ናቸው። የእባቡ ሠፈር ቅኔዎች የዲያቢሎስና የሞት ምሳሌዎች ናቸው። የእግዚአብሔር ከተማ ጽዮን በአንድ በኩል፤ የዲያቢሎስ ከተማ ባቢሎን በሌላ በኩል፣ የቅዱሳን ሠፈር ምስራቅ በአንድ በኩል፤ የዲያቢሎስ ሠፈር ምእራብ በሌላ በኩል - ይህን ነው እንግዲህ የእግዚአብሔር አምላክ ነቢያት በእግዚአብሔር መጽሐፍ፥ በተለያዩ የትውልድ ዘመናትና በተራራቁ ሥፍራዎች፥ በልዩ ልዩ ምሳሌዎች ያሠፈሩት። 

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም።

የእግዚአብሔር አምላክ መጽሐፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በየገጹ አክብሯታል።  ማንም ፍጥረት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ክብር ነስቶ የክርስቶስ ወገን ከቶ ሊሆን አይችልም። በመጽሐፍ ቅዱስ የጌታችን የመዳህኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ባለበት ሁሉ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ አለ። በእግዚአብሔር አምላክ መጽሐፍ ከብዙው በጥቂቱ እመቤታችን በሚከተሉ ምሳሌዎች ተገልጻለች።

የኖህ
 መርከብ። [፭]

የምድር ፍጥረት በሷ በኩል እንዲድን በእግዚአብሔር የተዘጋጀች [፮] ፣ የሥጋዊ ነገር ማእበል - ሞገድ የማይነቀንቃት፥ የሥጋዊ ፈቃድም ነፋስ ኃይል የማያዘነብላት መርከብ።[፯]

የወይራ ቅጠል የተሸከመችው
እርግብ። [፰}

ኖህ… እርግብንም እንደገና ከመርከብ ሰደደ። እርግብም በማታ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለሰች። በአፏም እነሆ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ነበር። ኖህም ከምድር ላይ ውኃ እንደቀለለ አወቀ። [፱] እርግቧ የወይራ ቅጠል ተሸክማ ወደ መርከቡ ነዋሪዎች መጥታ የምሥራቹን እንዳበሰረች፣ እነሆ ድንግልም የምሥራቹን ክርስቶስ በማህጸኗ ተሸክማ ለምድር ነዋሪዎች ነጻነትን አበሰረች። 

ሙሴ የተገኜባት የደንገል ሳጥን።
[፲]

የፈርኦን ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ በወረደች ጊዜ  በወንዙ ዳር በቄጠማ ውስጥ የደንገል ሳጥን አየች፥ ደንገጠሮቿንም ልካ ሳጥኑን አስመጣችው። በከፈተችውም ጊዜ ሕጻኑን አየች፥ ሕጻኑ ያለቅስ ነበር። ይህ ሕጻን አድጎ  በባርነት ውስጥ የነበሩትን የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ የግፍ ቀንበር በእግዚአብሔር ሃይል ነጻ ያወጣው ሙሴ ነበር። ሙሴ የጌታችን የመድኃኒታችን የክርስቶስ፣ የደንገል ሳጥኑ ደግሞ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌዎች ናቸው።
 
የኮሬብ
 ቁጥቋጦ። [፲፩]

እግዚአብሔር አምላክ በሐመልማል
እና በነበልባል የተዋህዶን፥ የክርስቶስን ምሳሌ በኮሬብ ተራራ ለሙሴ ገለጠለት። ሐመልማል የሥጋ፥ ነበልባል የመለኮት ምሳሌ ነው። በኮሬብ ተራራ እሳት ተሸክማ ያልተቃጠለችው ይህች እፅ የድንግል ማርያም ምሳሌ ናት።

የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት።
[፲፪]

እግዚአብሔር አምላክ ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፥ ከግራር እንጨት ታቦትን ሥሩ። በታቦቱ ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ አለው። በታቦቱ ውስጥ አሥሩ የእግዚአብሔር ቃላት ያለበት ጽላት ይቀመጣል።  ይህ ቃል ሥጋ የመሆኑ ምሳሌ ነው። በታቦቱ ውስጥ ያለው ምስክር የክርስቶስ፣ ታቦቱ የድንግል ማርያም ምሳሌዎች ናቸው።

የአሮን
 በትር። [፲፫]

የእስራኤል ልጆች ባጉረመረሙ ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ እያንዳንዱ ከየአባቶቻቸው ቤት አንዳንድ በትር እንዲያመጡ ሙሴን አዘዘው።  መሴም እንደተባለው አደረገ። ሙሴም ወደ ምክክሩ ድንኳን ውስጥ በገባ ጊዜ የአሮን በትር አቆጠቆጠች፣ ለመለመችም። አበባም አወጣች፥ የበሰለ ለውዝም አፈራች። ከሌሎች ተለይታ ያቆጠቆጠችው ይህች የአሮን በትር ከሴቶች ሁሉ ተለይታ የተባረከችው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት።

የጌድዮን
 ጸምር። [፲፬]

ጌዲዮን እግዚአብሔርን ጠየቀ። እነሆ ባውድማው ላይ የተባዘተ የበግ ጠጉር አኖራለሁ፥ በጠጉሩ ብቻ ላይ ጠል ቢሆን፤ በምድሩም ሁሉ ደረቅ ቢሆን እንደተናገርህ የእስራኤልን ልጆች በእኔ እጅ እንድታድናቸው አውቃለሁ አለ። እንዲሁም ሆነ።  ጠል ያረፈበት ጸምር የእመቤታችን ምሳሌ ነው። ጠል የመለኮት ምሳሌ ነው።


የሰሎሞን
 ዙፋን። [፲፭]

ንጉሡ ሰሎሞን የክርስቶስ ምሳሌ ነው። እሱን የተሸከመው ዙፋን የድንግል ማርያም ምሳሌ ነው። እንደገናም የሰሎሞን እናት ቤርሳቤህም የክርስቶስ እናት የሆነችው የድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። ቤርሳቤህ ማለት ቃል ኪዳን ሲሆን የኪዳነ ምህረት ምሳሌ ነው። የክርስቶስ ምሳሌ የሆነው ሰሎሞን ወንበር አስመጥቶ የድንግል ማርያም ምሳሌ የሆነችውን እናቱን ቤርሳቤህን በቀኙ አስቀመጣት።  የሰሎሞን አባት ውዱ ዳዊትም ለንግሥቷ ድንግል ማርያም በትንቢት ዘመረ፥ እንዲህም አለ፥ በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች። [፲፮] እንደገናም እግዚአብሔር በቅድስት ድንግል ማርያም ማህጸን እንዲያድር እንደወደደ፥ ልጄ ሆይ ስሚ፣ እይ፣ ጆሮሺንም አዘንብይ፣ ወገንሺንም፣ ያባትሺንም ቤት እርሺ፥ እርሱ ውበትሺን ወዷልና፣ እርሱ ጌታሽ ነውና። [፲፯]  

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ስለሆነችው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም   መጽሐፍ ቅዱስ የምሳሌ ምስክርነት እንደ ወንዝ ያፈሳል። ከብዙ በጥቂቱ፥  የእስራኤል መና፣ የአሚናዳብ
ሠረገላ፣ የያእቆብ መሰላል፣ የኤልሳእ ማሠሮ [፲፰] ፣ አቤኔዘር የተባለች የረድኤት ድንጋይ [፲፱] ፣ የቄርሜሎስ መሠዊያ [፳] ፣ የእግዚአብሔር ዳመና [፳፩]፣ የእግዚአብሔር ከተማ  [፳፪]፣ የይስሃቅ በረከት፣ ጠል የሚወርድባት እርሻ፣ የሊባኖስ እንጨት [፳፫]፣ ሙሽራ [፳፬] ፣ የተቆለፈች ገነት [፳፭]፣ የተዘጋ ምንጭ [፳፮]፣ የታተመች ፈሳሺ [፳፯] ፣ የሮማን መብቀያ [፳፰] ፣የተመረጠ ፍሬ መብቀያ [፳፱]፣ ቆዕ ከናርዶስ ጋር ያለባት ገነት [፴] ፣ ናርዶስ ከቀጋ ጋር [፴፩]፣ የሺቱ ሳር [፴፪] ፣ የሺቱ ቀረፋ  [፴፫]፣ የገነት ምንጭ [፴፬] ፣ የሕይወት ውኃ ጉድጓድ [፴፭]፣ እንዳንዶቹ ናቸው።

ቅዱሳን አባቶቻችን ለዘመናት ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደተማሩት ክርስቶስን ስለወለደችልን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ሲቀኙ ኖረዋል። ቅዱሳንም እግዚአብሔር አምላክ ባወጣላት ስሞቿ፥ የእግዚአብሔር ቤት [፴፮] ፣ ለዘላለሙ የማትፈርስ፥ የማትወድቅ - ፀንታ የምትኖር አዳራሽ - ለዘወትርም አጥሯ፣ ቅጥሯ የማይፈርስ [፴፯]፣ የሱፍ
እንጨት፣ የወይን ሃረግ፣ መሶብ፣ የዳዊት መሰንቆ፣ የያሬድ ዝማሬ፣ ከተራራ በረድ የሚነጻ የጴዴሬና የኤሞዳ እንቁ ድንጋይ፣ ኆኅተ ምሥራቅ፣ የቤተመቅደስ ቃጭል፣ ቤተልሄም፣ በረት፣ ጽዮን፣ የጽዮን ልጅ፣ ኢትዮጵያ - እያሉ ተቀኝተውላታል።

ቅድስት ድንግል ማርያም በጽዮን ለምን ተመሰለች?  ጽዮን የእግዚአብሔር ታቦት ያረፈባት የዳዊት ከተማ እግዚአብሔር አምላክ ደጇን ከሁሉም በላይ ወዷልና የተመረጠች ናት። ከፍጡራን ሁሉ ለይቶ እግዚአብሔር በማህጸኗ ለማደር ቅድስት ድንግል ማርያምን መርጧልና እሷ የተባረከች የእግዚአብሔር ከተማ ናት።

የእግዚአብሔር ታቦት ያረፈባት የእግዚአብሔር ከተማ ኢትዮጵያ እነሆ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፈሪሳውያን አይሁዶች የእግዚአብሔር መንግሥት ከናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ህዝብ ትሰጣለች [፴፰] ብሎ የተቀኜላት የጽዮን ልጅ ናት። የዳዊት ከተማ ምሱላዊ፣ ብሔረ ኢትዮጵያ መንፈሳዊ የጽዮን ምሳሌዎች ናቸው። ኢትዮጵያ የድንግል ማርያም ምሳሌ፣ የእግዚአብሔር ከተማ ጽዮን የተባለችባቸው ምክንያቶች አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው።

ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ
[፴፱]

በአሁኑ ዘመን ያሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ አገር ሰዎች የኢትዮጵያ ነገሥታት ከስማቸው በፊት "ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ" የሚል አነጋገር ለምን እንደሚጨምሩ አያውቁም። አንዳንዶቹ አፄ ኃይለ ስላሴ እራሳቸውን የይሁዳ ዘር ማለታቸው ነው ብለው በፈቃዳቸው ይተረጉሙታል። የውጭ አገር ተራኪዎችም ትርጉሙን ሳያውቁ እስከ አሁኑ ሰዓት ድረስ፣ መጽሐፍ እስኪጽፉበትም ድረስ ትርጉም ሲያሳጡት እናያለን። ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ በብሉይ ኪዳን በኦሪት ዘፍጥረት ያእቆብ በትንቢት የተናገረለት፣ በአዲስ ኪዳን ደግሞ በዮሃንስ ራእይ በሰባት ማህተም የተዘጋውን መጽሐፍ የሚከፍተው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የኢትዮጵያ ነገሥታት ከስማቸው በፊት ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ የሚለውን ቃል የሚጠቀሙበት ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን በአርእስቱ ማስፈር ስላለባቸው ነው። ነገሥታቶቹ  ቦታውን ለመያዝ ንጉሥ ይባሉ እንጂ ዋናው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። አጼ ኃይለ ስላሴም ከስማቸው በፊት፣ ከእሳቸው በፊት የነበሩ ንጉሦችም፥ ዳግማዊ አጼ ምኒልክም፣ ሰማእቱና ታላቁ ንጉሥ አራተኛው አጼ ዮኃንስም፣ ሌሎችም እንዲሁ ከስማቸው በፊት ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ የሚል ቃል ከማእረገ ንግሥና ስማቸው አስቀድሞ ሠፍሯል። ኢትዮጵያን ከሌሎች አገሮች የተለየች የሚያደርጋትም አንደኛው ሚስጢር ይሄ ነው። አብርሃ ወ አጽብሃ ክርስትና የኢትዮጵያ ኃይማኖት ነው፣ የኢትዮጵያም ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲሉ አዋጅ አወጁ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን፥ ከንጉሡ እስከ ገበሬው፣ ከአዛውንት እስከ ህጻናት፣ ከሊህቅ እስከ ደቂቅ ድረስ፥ ንጉሣቸውን ኢየሱስ ክርስቶስን በማለዳ ተነስተው እያወደሱ፣ በሕጉም እየሄዱ ኖሩ። የኢትዮጵያን ታሪክ ለመመርመር ለሚሹም ይህ ለኢትዮጵያ ሕልቆ መሳፍርት የሌለው በረከትን እንዳጎናጸፋት ማየት ይችላሉ።

በምድር ላይ በእግዚአብሔር ፈቃድ በሰዎች ምርጫ በቤተ መንግሥት አዋጅ ክርስቶስ ለረጂም ጊዜ የነገሠባት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት። የንጉሡ የክርስቶስ ዙፋን ናትና የድንግል ማርያም ምሳሌ ኢትዮጵያ ጽዮን ትባላለች። በዚህ ዘመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዲያቢሎስ አማካሪነት ከታሪካቸው ተለይተዋልና አያውቁትም እንጂ ኢትዮጵያ ጽዮን፣ ንጉሡም የጽዮን ንጉሥ ይባሉ ነበር። ይህም በታሪከ ነገሥትና በሌሎችም መጻሕፍቶች ተጽፎ ይገኛል። የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ የኹኖ አምላክ እስከ ዐፄ ልብነድንግል በሚለው መጽሐፋቸው ተክለ ጻድቅ መኹሪያ ስለ ኢትዮጵያ ነገሥታት የአክሱም የቅብዐ ንግሥ ሥርዓት የጻፉትን በአጭሩ እንይ፥

"… የራሱን ጠጉር ቆርጠው ቀሳውስትና ዲያቆናት ከጥና ጋር ወስደው ፫ ጊዜ ታቦቱን ይዞሩና መልሰው አምጥተው የነገሥታት መማፀኛ ደንጊያ በሚባለው ላይ ያስቀምጡና በላዩ ላይ ከጥናው ውስጥ ያለውን የሳት ፍሕም አፍስሰው ንጉሡን እግዚአብሔር አይለይህ፣ እግዚእትነ ማርያም ትርዳህ … ትርዳህ ብለው አማፅነው ሺህ ዓመት ያንግሥህ ብለው ሲመርቁትና ከዚያ እምቢልታ ነጋሪት መመታት ሲጀምር ግርግሩና እልልታው ይቀልጣል። ቀጥሎ ንጉሡ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ሰውነቱን ያማፅናል።

"ከዚያ ይወጣና  ዛሬም ግማሾቹ በአክሱም እንደሚታዩት የእስራኤል ልጆች (ዳኞች) በሚቀመጡበት ፲፪ የደንጊያ ወንበር በሚባለው፥ ፮ቱን በቀኝ፣ ፮ቱን በግራ አድርጎ በመካከል ይቆማል። በዚያ ሳለ ጳጳስ፣ ቀሳውስት፣ ካህናት፣ ዲቆናት ከፊቱ እየመጡ ሺህ ዓመት ያንግሥህ ይሉታል።

"የተተከለ ደንጊያ ባለበት (ምዕራፍ) በምሥራቅ በኩል ወደ አክሱም ሲመጣ  ሕግ አዋቂዎች፣ ሹማምንት፣ ሠራዊት በየወገናቸው ሆነው ይቀበሉታል። ደናግል ሴቶች የቀይ ሐር መጋረጃ በቀኝና በግራ ይዘው መንገዱን ይዘጉበታል። ከልጃገረዶቹ አንዲቱ አንተ ማነህ ብላ ትጠይቀዋለች። እሱም ንጉሥ ነኝ ይላታል። አይደለህም ትልና እንደገና አንተ ማን ነህ ብላ ስትጠይቀው፥ ንጉሥ ነኝ ይላታል፤ ጥያቄውና መልሱ ሁለት ጊዜ ከተደጋገመ በኋላ በ፫ኛው አንተ ማን ነህ ስትለው ሰይፉን መዞ የሐሩን መጋረጃ ይቆርጠውና የጽዮን ንጉሥ እኔ ነኝ ይላታል። በዚያን ጊዜ የጽዮን ንጉሥ በእውነት በእውነት (አማን በአማን) ስትለው ሕዝቡም እርሷን ተከትሎ የጽዮን ንጉሥ … ይለዋል" [፵]        
  
   
ዝማሬ መላእክት

ኢትዮጵያ ጽዮን ተብላ የምትጠራበት ሌላው ምክንያት እግዚአብሔርን ታመሰግንበት ዘንድ ከአገሮች ሁሉ ተለይታ ዝማሬ መላእክት ስለተሰጣት ነው። ይህ ዝማሬ ያሬዳዊ ዜማ ነው።  እግዚአብሔር ይህን ዝማሬ ከኢትዮጵያ በቀር ለማንኛውም አገር አልተሰጠም። ዝማሬ መላእክት ተለይቶ ለኢትዮጵያውያን መሰጠት ቀላል ነገር አይደለም - እጅግ በጣም እጹብ ድንቅ የሆነ ጸጋ ነው እንጂ። ህጻኑ ንጉሥ ክርስቶስ በበረት ውስጥ በቤትልሔም ሲወለድ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርን እያመሰገኑ - ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ እያሉ ለእረኞች አበሰሩላቸው። [፵፩]

የመላእክት ዝማሬ ከሌሎች ተለይቶ የተሰጣት ከሌሎች አገሮች ተለይታ እግዚአብሔርን ንጉሥ አድርጋ የተቀበለች በመኾኗ ነው። አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ሌሎች አገሮች ይህ ዜማ ስለሌላቸው እኛ የሌሎችን ፒያኖና የሙዚቃ አይነቶች እንጠቀም እያሉ ሲፈላሰፉ ይሰማሉ። ይህ እስራኤል ዘስጋ የእግዚአብሔርን መና ንቀው የግብጽን ፍርፋሬ እንደሻቱት አይነት ስድብ ነው። ሰው እግዚአብሔር መርጦ የሰጠውን ንቆ ሌላ የሚሻበት ምክንያት ምንድን ነው?  ሌሎች የላቸውምና እኛ እነሱን እንምሰል የሚል ፍልስፍና ውስጥስ የሚያስገባ ምን ችግር መጣ?        

የባቢሎን ከበባ

ኢትዮጵያን ጽዮን የሚያሰኛት ሌላው ምክንያት ኃይማኖቷን በሚጻረሩ በግብጽና በባቢሎን መከበቧ ነው። በተለይም በመጨረሻው ዘመን ዳር ድንበሯ በባቢሎን እንደሚያዝ፣ የባህር በሮቿ በባቢሎን እንደሚዘጉባት፣ የባቢሎን ኃይማኖቶች መጥተው የተመረጡትን ብላቴናዎቿን እንድሚያስቱ የእግዚአብሔር ነቢያት አስቀድመው ስለተነበዩ እና ይህም በኢትዮጵያ ላይ ስለሚፈጸም ነው። በትንቢተ ዳንኤል የባቢሎን አኪያሄድ የተጻፈው በተለይ በዚህ ዘመን ያለ ሰው በቀላሉ በሚረዳበት መንገድ ነው። በምድር ላይ የሚነሳው አራተኛው ንጉሥ ወይም አውሬ ወይም አገር (ከግሪክ የሚጀምረው የምዕራብ የበላይነት) በተነሳ ጊዜ መንግሥቱ እስከ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ይከፋፈላል። የደቡቡ ንጉሥ (የፈረንሳይን ታሪክ ያንብቡ) እና የሰሜኑ ንጉሥ (የእንግሊዝን ታሪክ ያንብቡ) እየተቀያየሩ የሚሸናነፉበት ረጂም ጦርነት ያደርጋሉ (የ፻ አመቱ ጦርነት በመባል የሚታወቀውን የፈረንሳይና የእንግሊዝ ጦርነት ታሪክ ያንብቡ) የደቡብም ንጉሥ ሴት ልጅ (ጆዋን ኦፍ አርክ የተባለችውን የፈረንሳይ ልጅ ታሪክ ያንብቡ) ቃል ኪዳን ለማድረግ ወደ ሰሜን ንጉሥ ትመጣለች። የክንዷ ኃይል ግን አይጸናም። እርሷና እርሷን ያመጡ፥ የወሰዳትም በዚያም ዘመን ያጸናት አልፈው ይሰጣሉ። ከስሯ ቁጥቋጥ አንዱ (የናፖሊዮንን ታሪክ ያንብቡ) በስፍራው ይነሳል። ወደ ሠራዊቱም ይመጣል። ወደሰሜንም ንጉሥ አምባ ይገባል። ከብርና ከወርቅ የተሠሩትን እቃዎች ይዞ ወደ ግብጽ ይማርካል። ግብጽ ከደቡቡ ንጉሥ ወጥታ በሰሜኑ ንጉሥ እጅ ትወድቃለች። የደቡቡና የሰሜኑ ንጉሥ በአንድ ጠረጴዛ ሆነው ይወሻሻሉ። ሁለቱም ወደ መልካሚቱ ምድር (ጽዮን ) ያመራሉ። መልካሚቱን ምድር ይከባሉ (የእንግሊዝና የፈረንሳይን የኢትዮጵያ ከበባ በሱዳን፣  በሶማሊያ፣ በጂቡቲ ወዘተ ያንብቡ)።

ይህን ትንቢት ነቢዩ ዳንኤል የጻፈው የዛሬ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ አመት አካባቢ ነው። ታሪኩ የሌላ ነው እንዳይባል ታሪኩ የተፈጸመው በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ነው።

የባቢሎን ሰዎች ፈልገውም ቢሆን የጽዮን ወዳጅ ሊሆኑ አይችሉም። በባቢሎን የሚቋጨው ሥርአትም ሆነ የሚደረገው ግብር እያንዳንዱ ጽዮንን የሚጻረር ነው የሚሆነው። ጽዮንም ከባቢሎን ጋር ወዳጅነትን ብትሻ የባቢሎን ሰዎች ያፌዙባታል እንጂ ወዳጅ ሊሆኗት አይችሉም። ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያን እጃቸውን ቢዘረጉላቸውም እንኳን ምእራባውያን ኢትዮጵያን በጠላትነት እንጂ በወዳጅነት ሊያይዋት ከቶ የማይችሉት። በባቢሎን ምድር የሚደረግ የጽዮን ዝማሬም ትርፉ በረከት ላይሆን ይችላል። ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ አለ፥ በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፣ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን። በአኻያ ዛፎቿ ላይ መስንቆቻችን ሰቀልን። የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን። የወሰዱንም፥ የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን። የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባእድ ምድር እንዴት እንዘምራለን ? [፵፪]      
     
ስለ ድንግል ማርያም ተቃዋሚዎች

የድንግል ማርያም ተቃዋሚዎች በአሁኑ ጊዜ በብዙ በተለያዩ መንገዶች እና በረቀቀ አቀራረብ ሲቀርቡ እናያለን። ከላይ ከመጀመሪያ እንዳየነው እግዚአብሔር አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን አሳቾች የምንለይበትን ምልክቶች አስቀድሞ አዘጋጅቶልናል።

እባብ ሴቷን ለማሳት ወደ ገነት መጣ እንጂ እሷ ወደ እባቡ አልሄደችም። ይህ አንዱ መለያ ነው። የባቢሎን ፓስተሮች ወደ ጽዮን መጥተው ድንግል ማርያም አታማልድም፣ እናትና አባቶቻችሁን አትስሙ፣ ኢየሱስም ያለው ከኛ ጋር ነው ፣ ኑ የግል አዳኝ አድርጋችሁ ተቀበሉት፣ እያሉ እጅግ ብዙ ብላቴናዎችን  ከኃይማኖት አስወጥተዋል። ኢትዮጵያውያን ክርስቶስን እንደሚያመልኩ እያወቁ፣ የናንተ አምልኮ ልክ አይደለም፣ የኛን ተቀበሉ ብለው እባብ ወደ ገነት መጥቶ ሴቷን ከአባቷ እንደለያያት እነሱም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው፣ አባትና ልጅን፣ እናትና ልጅን፣ እህትና ወንድምን በሃይማኖት ለያይተዋል፥ ያውም በማርያም ጥላቻ። ኢትዮጵያን ከፋፍለዋል፣ በባቢሎን እንድትወረር፣ መውጫ መግቢያም እንድታጣ መንገዱን ዘግተዋል። ይህ አንዱ መለያ ነው።

የተዋህዶ ሰዎች መስለው የባቢሎንን እምነት በተዋህዶ ብላቴኖች ውስጥ ለውስጥ ለመጫን በቤተክርስቲያን ውስጥ ያደፈጡ የተሃድሶ አራማጆችም እንደዚሁ እንደ እባቡ አስመስለው ወዳጅ መስለው ገብትዋልና ወደ ውይይት እንኳን ሳይገባ በዚህ እግዚአብሔር በተወልን ምልክት የዲያቢሎስ ወገን መሆናቸውን መለየት ይቻላል። የእግዚአብሔርን  እውነት የያዘ ፊት ለፊት በበር እንጂ በመስኮት፣ በድብቅ፣ በማጭበርበር አይገባምና። 

ቅድስት ድንግል ማርያም ጥላሸት አለባት ካላልን ሞተን እንገኛለን የሚሉ ደግሞ ትልቅ ችግር አለባቸው። በመጀመሪያ ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር እናት ናት የሚለውን የተዋህዶ እምነት እንኳን ካቲሊኮች የተቀበሉት በስድስተኛው ምእተ አመት ነው።  ካቶሊኮች ከተዋህዶ ሊወስዱ ይችላሉ እንጂ ተዋህዶ ከካቶሊኮች እምነት አልትዋሰችም። ቁም ነገሩ ይሄ አይደለም። የተዋህዶ መጻሕፍት እና ቅዱሳኖቿ የሚሉት እግዚአብሔር ቅድስት ድንግል ማርያምን ንጹህ አድርጎ አዘጋጅቶ በማህጸኗ አረፈባት ነው የሚሉት። ጥላሸት ካልቀባን የሚሉ ሰዎች ደግሞ ንጹህ ያደረጋት በማህጸኗ ከማረፉ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ነው እንጂ በናቷ ማህጸን ሳለች አይደለም ይላሉ። ይህን የሚሉት እሷ ጥላሸት ከሌለባት ከሌሎች ሰዎች ጋር አብሮ አላዳናትም ማለት ነው የሚል ፍልስፍና ውስጥ ለመግባት ነው። አሁን የነዚህ ሰዎች ችግር እዚህ ላይ ነው። በሶስተኛው ቀን ነው ከመቃብር ሲነሳ ክርስቶስ ሞትን የሻረው። ንጹህ ያደረጋት ልክ ሊራፍባት ሲል ነው የሚሉ ሰዎች እነሱ በሚሉትም መንገድ የፍልስፍናቸው ጥያቄ ሊቀየር አይችለም። ክርስቶስ በማህጸኗ ሊያርፍባት ሲልም፣ ሲያርፍባትም፣ ሲወለድም፣ ሲያድግም ገና አልሞተም፣ ገና ሞትን ሽሮም አልተነሳም ነበር። እነዚህ ሰዎች ክርስቶስ ሊያርፍባት ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው አንጽቶ ከተወለደ በኋላ እንደገና መልሶ ጥላሸት አስቀመጠባት ካላሉ በቀር ፍልስፍናቸው አእምሯቸውን ሲያዞረው ይኖራል።  እግዚአብሔር ደግሞ ያነጻውን ጥላሸት መልሶ የሚቀባ አምላክ አይደለም። ለድንግል ማርያም ምሳሌነት ሴቷን ሄዋንን ያዘጋጀ አምላክ ድንግል ማርያምን ያዘጋጀው ገና ያን ጊዜ መሆኑን፥ ከሴቷ የሚወለደው የእባቡን እራስ ይቀጠቅጣል ሲል ገና ከጅምሩ ነግሮናል። ቅዱስ ገብርኤል ሲያበስራት እንደቃልህ ያድርግልኝ በማለቷ ንጽህናን ያገኘችው ያን ጊዜ ነው ማለት አይደለም። እግዚአብሔር አምላክ ዳዊትን ለንጉሥነት ያዘጋጀው ገና ዳዊት ሳይወለድ ነው። ሳሙኤል ቅባ ቅዱስ የቀባው ሥርአቱ እንዲፈጸም እንጂ ዳዊት የተመረጠው በዛች ደቂቃ ነው ማለት አይደለም። እንዲሁም የእግዚአብሔር በትረ መንግሥት ከእሥራኤል ዘስጋ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚዞር እግዚአብሔር አምላክ ምሳሌን ያዘጋጀው በመልከጼዴቅ ክህነት ሲሆን ኢትዮጵያዊው ንጉሥ የሰሎሞንና የሳባ ንግሥት ልጅ ዳዊት (ቀዳማዊ ምኒልክ) በሌዋዉያን የቅዳሴ ሥርአት ተማፅኖ የኢትዮጵያ ንጉሥ ተብሎ በእስራኤል አገር የዳዊትን ቅባ ቅዱስ ሲቀባ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ ዞረች። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ኢትዮጵያውያንን በእስራኤላውያን ማህበር እናይ ነበር።

ቅዱሳን ሞተዋልና አያማልዱም ለሚሉም ቅዱሳን ህያው መሆናቸውን ይወቁ። ቅዱሳን ሞተዋል የሚሉ እነሱ እራሳቸው ሞተዋል ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ሺሮ  የህይወትን መንገድ እንደሠራ አላመኑምና።  የባቢሎንን ትምህርት ተውሰው በአፀደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን በአንድ ጊዜ ብዙ ቦታ መገኜት አይችሉምና የሁላችሁንም ጸሎት ሊሰሙ አይችሉምና ቅዱሳን እንዲያማልዷችሁ አትጸልዩ ለሚሉ ደግሞ ቅዱሳን የሚሠሩት በመንፈስ ቅዱስ ነው። ለመንፈስ ቅዱስ ማጓጓዣ የሚሳነው አለን? እንደ ባቢሎን ፍልስፍና ቢሆንማ ኖሮ የፍጥነት ሁሉ መጨረሻ የብርሃን ፍጥነት ነው ስለሚባል ቅዱስ ገብርኤል ከሰማየ ሰማያት መልእክት ይዞ ድንግልን ለማብሰር ወደ መሬት ሲመጣ ዓለም ሳትፈጠር ተነስቶ ዓለም ከጠፋች በኋላም አይደርስም ነበር።            

የእግዚአብሔር መጽሐፍ ሲጀመር በኦሪት ዘፍጥረት ሲደመደምም በዮኃንስ ራእይ የሰጠን ዋነኛ ምልክት እባብን የምንለየው በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ ሲያነጣጥር ነውና፣ ኢትዮጵያም የድንግል ማርያም ምሳሌ፣ የክርስቶስም ልብስ ናትና፤ እባቡ በኢትዮጵያ ላይ ካነጣጠረ ቆይቶአልና፡ የኢትዮጵያን ዙሪያ ከቧልና፣ ድንኳኑንም በተራሮቿ ላይ ተክሏልና፣ መውጫ መግቢያዋንም ዘግቷልና፣  ኢትዮጵያውያን ለራሳቸው ሲሉ ከድንግል ማርያም ተቃዋሚዎች መራቅ አለባቸው። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን የሚጠብቀው ኢትዮጵያውያን ድንግል ማርያምን በክብር ስንጠብቅ ብቻ ነው።

ሊቁ ጻዲቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ብዙ ተቀኝተዋል። እንዲህም አሉ፥ የድንግል ማህጸን ፍሬ ክርስቶስ በቤተክርስቲያን ተሞሸረ፣ የክርስቶስ ምእመናን ከቤተክርስቲያን ተጸነሱ። [፵፫] ክርስቶስም ፥ ለመታረድ የማያቋርጥ፣ እርዱ የማያልቅ ንጹሕ ላህም [፵፬] ነው አሉ። ሊቁም አሉ፥ ቅድስት ድንግል ማርያም ከርኩሰትም ሁሉ ንጽሕት፣ ከኃጢአትም ሁሉ የጸራች እንደሆነች የማያምን እርጉም ነው። ]፵፭] ሰይጣን በድንግል ማርያም ታመመ፣ በልጇ ተጨነቀ፣ በልጇ መስቀል ስቃይ አገኘው። ስለዚህም ከፍጡራን ወገኖች ሁሉ ሰይጣን ቅድስት ማርያምን ይጠላል። [፵፮]


እግዚአብሔር አምላክ ይመስገን።
የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ ኢትዮጵያን አይለያት።


ሙሉጌታ


 ሁለተኛው የሐዋርያው የጴጥሮስ መልእክት፣ ም ፩ ፣ ከቁ ፳ እስከ ፳፩
 ኦሪት ዘፍጥረት ም ፳፪ ፣ ቁ ፱
  ኦሪት ዘፍጥረት ም ፳፪ ፣ ቁ ፲፪ እስከ ፲፬
  ኦሪት ዘፍጥረት ም ፪ እና ፫
 ኦሪት ዘፍጥረት ም ፯ ፣ ቁ ፲፰
  ኦሪት ዘፍጥረት ም ፮ ፣ ቁ ፲፭
  ጻዲቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ መጽሐፈ አርጋኖን፣ ም ፫ ፣ ቁ ፵፬
 ኦሪት ዘፍጥረት ም ፰ ፣ ቁ ፲፩
  ኦሪት ዘፍጥረት ም ፰ ፣ ከቁ ፲ እስከ ፲፪
  ኦሪት ዘጸአት ም፪ ፣ ቁ ፫
 ፲፩ ኦሪት ዘጸአት ም፫ ፣ ቁ ፫
 ፲፪ ኦሪት ዘጸአት ም፳፭፣ ቁ ፲
 ፲፫ ኦሪት ዘኁልቁ ም፲፯፣ ቁ ፰
፲፬  መጽሐፈ መሳፍንት፣ ም ፮፣  ከቁ ፴፮ እስከ ፴፱
፲፭ መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ም፪ ፣ ቁ ፲፱
፲፮  መዝሙረ ዳዊት ም ፵፬ ፣ ቁ ፱
፲፯  መዝሙረ ዳዊት ም ፵፬ ፣ ቁ ፲ እስከ ፲፩
፲፰  መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ም፪ ፣ ቁ ፲፱
፲፱  መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ ም፳፬ ፣ ከቁ ፲፰ እስከ ፳፭
   መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ፣ ም፲፰ ፣ ቁ ፴፰ 
፳፩ ትንቢተ ኢሳያስ፣ ም፲፱ ፣ ቁ ፩
፳፪  መዝሙር ፹፮ ፣ ቁ ፫
፳፫  መኃልየ ማኅልይ ዘሰሎሞን፣ ፣ ቁ
፳፬ መኃልየ ማህለይ ዘሰሎሞን፣ ፬ ፣
፳፭  መኃልየ ማኅልይ ዘሰሎሞን፣ ፬ ፣ ፲፪
፳፮  መኃልየ ማኅልይ ዘሰሎሞን፣ ፬ ፣ ፲፪
፳፯ መኃልየ ማኅልይ ዘሰሎሞን፣ ፬ ፣ ፲፪
፳፰ መኃልየ ማኅልይ ዘሰሎሞን፣ ፬ ፣ ፲፫
፳፱  መኃልየ ማኅልይ ዘሰሎሞን፣ ፬ ፣ ፲፫
  መኃልየ ማኅልይ ዘሰሎሞን፣ ፬ ፣ ፲፫
፴፩  መኃልየ ማኅልይ ዘሰሎሞን፣ ፬ ፣ ፲፬
፴፪  መኃልየ ማኅልይ ዘሰሎሞን፣ ፬ ፣ ፲፬
፴፫ መኃልየ ማኅልይ ዘሰሎሞን፣ ፬ ፣ ፲፬
፴፬  መኃልየ ማኅልይ ዘሰሎሞን፣ ፬ ፣ ፲፭
፴፭  መኃልየ ማኅልይ ዘሰሎሞን፣ ፬ ፣ ፲፭
፴፮  ጻዲቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ መጽሐፈ አጋኖን፣ ም ፭ ፣ ክፍል ፲፭ ፣ ቁ ፱
፴፯  ጻዲቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ መጽሐፈ አርጋኖን፣ ም ፫ ፣ ቁ ፵፬
፴፰  የማቴዎስ ወንጌል ም ፳፩ ፣ ቁ ፵፫
፴፱  ኦሪት ዘፍጥረት ም ፵፱ ፣ ከቁ ፰ እስከ ፲፪ ፣ የዮኃንስ ራእይ ም ፭ ፣ ቁ ፭
  ተክለ ጻድቅ መኹሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ፪ኛ መጽሐፍ፣ ገጽ ፻፵
፵፩  የሉቃስ ወንጌል ም ፪ ፣ ከቁ ፲፫ እስከ ፲፬
፵፪ መዝሙረ ዳዊት ም ፴፯፣ ከቁ ፩ እስከ ፬
፵፫  ጻዲቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ መጽሐፈ አርጋኖን፣ ም ፯ ፣ ክፍል ፭፣ ቁ ፭ 
፵፬  ጻዲቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ መጽሐፈ አርጋኖን፣ ም ፱ ፣ ክፍል ፯፣ ቁ ፵
፵፭ ጻዲቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ መጽሐፈ አርጋኖን፣ ም ፬ ፣ ቁ ፱
፵፮ ጻዲቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ መጽሐፈ

ብፅእት።

 HOME