ስንዱ… 

ጥበብ፡ በድንኳንሽ፡ ያደረ፣
 ዋጋሽ፡ ከእንቁ፡ የከበረ፣
 ክንድሽ፡ ለትጋት፡ የበረታ፣
 እጅሽ፡ ለድሀ፡ የተፈታ፣
 ጣቶችሽ፡ እንዝርት፡ ይዘው፡ ዘርፍ፡ የቋጩ፣
ቤቶችሽ፡ በጽዮን፡ ሸማ -
      በእጥፍ፡ ድርብ፡ ነጠላ፡ የታጩ።
ስጋጃን፡ በእልፍኝሽ፡ ሠርተሽ፣
የበፍታን፡ ቀይ፡ ግምጃ፡ የለበስሽ፣
 አንደበትሽ -      በርኅራኄ፡ ህግ፡ የተገራ፣
 ጥበብን፡ በማለዳ፡ የጠራ።
 ልጆችሽ፡ ባንቺ፡ ብርታት ፣
በማለዳ፡ ተነስተው፣
ጥበብን -
      በአንደበታቸው፡ ጠርተው፣
የድግሽን፡ ሽያጭ፡ እየመነዘሩ፣
በሸንጎ  -
     ሥራሽን፡ ለብዙ፡ ዘመን፡ አወሩ።
 ስንዱ፦
ቀን፡ አለፈ፣
ምሽት፡ ከምሽት፡ ጀርባ፡ ተሰለፈ።
ሆነ፡ ማታ፣
እንደገናም፡ ምሽት፣
ጽኑ፡ ጨለማ፡ ውድቅት።

ውድቅትነቱን፡ አይታ ፣
መመሳሰልን፡ አጥንታ ፣
ነፍሳትን፡ በጎዳና፡ ልታጠምድ፣
ያዘጋጀች -
        የሚያዳልጥ፡ ብዙ፡ መንገድ፣
ከንፈሯ፡ ልዝብ፡ የማያፍር፣
ጨዋታዋ፡ ስሜትን፡ የሚያሰክር ፣
ቀበዝባዛ፣ 
የምታምር፡ ጋለሞታ ፣
ከባቢሎን፡ ተነስታ፡ መጥታ ፣
ከጎበዛዝት፡ መካከል፡ ገብታ ፣
ባልጋዋ፡ ሰርፍ፡ ዘርግታ ፣
አልሙና፡ ቀረፋም፡ ረጭታ ፣
የመውደድ፡ በሚመስል፡ ፈገግታ ፣
በጎዳና -
በየማእዘኑም፡  ጎትጉታ ፣ ጎትጉታ፣
በተሳለ፡ ምላስ፡ ወግታ ፣
ብላቴኖችሽን፡ በልታ፣ በልታ ፣
ቆላዎችሺን፡ ከደጋ፣
ባህሮችሽን፡ ከተራሮችሽ፡ ለይታ፣
ዙፋን፡ የጋራ፡ እንጂ፡ የውድሽ፡ አይሆንም፡ ብላ፣
እጅ፡ መንሻ፡ ጥላ፣
ጎበዛዞችሽን፡ ሸንግላ፣
ከመኳንንቶችሽ፡ ሰፈር፡ ገብታ፣
ምርጦችሽን፡ አስታ፣
የተቀደሰውን፡ አርክሳ፣
ላንቺም፡ መቃብር፡ ምሳ፣
ወንዞችሽን፡ አድርቃ፣
ዛፎችሽን፡ አጠውልጋ፣
ለባቢሎን፡ ርስት፡ ፈልጋ፣
ዘርግታለችና -
     ምላሷን፡ እስከ፡ ውድሽ፣
ድንኳኗን፡ እስከተራሮችሽ።
ስንዱ፡-
ስጋጃሽን፡ በእልፍኝሽ፡ አንጥፊና፣
የቀይ፡ ግምጃ፡ ልበሽና፤
ሸማሽን፡ አጣፊና፣
ዙፋኑን፡  አዘጋጅተሽ፡ እንደድሮው፤
በማለዳ፡ ጥበብን፡ ጥሪው፣
ውድሽን፡  ና ፦
እርስትህን፡ አድን፡ በይው።
ከባቢሎን፡ የመጣችው፣
መግቢያ፡ መውጫየን፡ የዘጋችው፣
የእልፍ፡ አእላፍን፡ የለት፡ መስዋእት፡ ያስቀረችው፣
ከቆምክበት፡ ቆማ፣
ቀንበር፡ በልጆቼ፡ ጭና፣
ርስትህን፡ ሺታለችና፣
አቅምም፡ ከልጆቼ፡ ሸሽቷልና፣
ላንተ፡ የሚሳንህ፡ የለምና፣
በይው፦
ውዴ፡  ና፣ ቶሎ፡ ና።


የባቢሎን፡ ቀንበር፡ በጽዮን።

 HOME