በአገር ውስጥ፣ በውጭ አገር፣ በየብስ፣ በባህር፣ በደጋ፣ በቆላ ወይም በወይናደጋ፣ በድሎት ወይም በመጠን ወይም በችግር ለምትኖሩ ኢትዮጵያዊ አንጋፋዎች፣ አዋቂዎች፣ ወንዶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ልጆችና ህጻናት በሙሉ። ሰላም ለናንተ ይሁን።

የዛሬ ሶስት ሺህ አመት በእግዚአብሔር እና በኢትዮጵያውያን መካከል  የተደረገውን በመጽሐፍ ተጽፎ የቆየውን ውል ተመልከቱ። የእግዚአብሔር ውል በሌዋውያን በኩል በሌዋውያን የክህነት እና የቅብዓተ ነገሥት አፈጻጸም ስርአት ተላለፈ። ስለኢትዮጵያ ደግሞ የዳዊት የልጅ ልጅ፣ የሰሎሞን ልጅ ዳዊት ወይም የኢትዮጵያ ንጉሥ ቀዳማዊ ምንሊክ ውሉን ተቀበለ።

ይህ ውል የዛሬ አንድ ሺህ ስድስት መቶ ሰማንያ አመት አብርሃና አጽብሃ በአዋጅ ክርስትናን የኢትዮጵያ ኃይማኖት ነው ብለው ሲያውጁ እና፡ በመንግሥት አዋጅና በአዲስ ኪዳን የቤተክርስቲያን የቅብዓተ ነገሥት ስርአት፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ለክርስቶስ ስትታጭ ዳግመኛ ጸና።      

እነሆ ኢትዮጵያውያን መልካም ቢሠሩ፣ እግዚአብሔር ባዘጋጀው መንገድ ቢጓዙ ይህን በረከት ያገኛሉ።

ምርቃት ለኢትዮጵያዊው፥

በመንገድህ፣ በአገርህ፣ በዱር፣ በቤትህ፣ በውጭ ሁሉ የተባረክህ ትሆናለህ።
የሆድህ ፍሬ፣ የምድርህ ፍሬ፣ የወንዝህ ምንጮች፣ የተክሎችህ ፍሬ፣ የከብትህ በረት፣ የበጎችህ መንጋ፣ ያከማቸኸው፣ ያተረፍከው ሁሉ የተባረከ ይሆናል።
ስትወጣና ስትገባ የተባረክህ ትሆናለህ።
እግዚአብሔር የሚቃወሙህን ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እንዲቀጠቀጡ ያደርጋቸዋል፣ እጅህን በጨመርክበትና በቤትህ ውስጥ በረከቱን ይልካል፣ በሆድህ ፍሬዎች በምድር እህል በከብቶቹ መራባት በመልካም ያበዛልሃል።
ለአባቶች በማለው ምድር የሰማይን ዘመን ያህል ይሰጥሃል።
እግዚአብሔር የሰማይን በረከት መዝገብ ይከፍትና የተባረከ ዝናብ ይሰጥሃል።
ለብዙ ህዝቦች ታበድራለህ። አንተ ግን አትበደርም።
በብዙ ህዝቦች ላይ ትፈርዳለህ። በአንተ ግን አይፈርዱብህም።
እግዚአብሔር ራስ አድርጎ ይሾምሃል እንጂ ጅራት አያደርግህም። በላይ እንጂ በታች አትሆንም።
ከሁሉ የምድር በረከትን ለእንስሶች ትሰበስባለህ። በከተማው ከአህዛብ ወገን የሆኑ ኣረመኔዎችን ትወስዳለህ። ስለ ክብርህ ከፍታ በምድር ላይ ያሉ ሁሉ ይሰግዱልሃል። ስምህ እንደ ዝግባ ከፍ ከፍ ይላል። የክብርህ ብርሃንም በምድር ላይ በሚኖሩ ህዝቦችና ወገንህ በሆነው በእስራኤል ህዝብ  ዘንድ እንደ ንጋት ኮከብ ያበራልሃል። እግዚአብሔር በመንገድህ ሁሉ ካንተ ጋር ይሆናል። ባሰብከውም ሁሉ ፈቃድህን ያደርግልሃል።
የጠላትህን አገር ትወርሳለህ። በግርማህ ብዛትና በሠራዊትህ የህዝብ ከፍታ ይመሰገናል። የእግዚአብሔርን ፈቃድ የማያደርጉ ሁሉ ይፈሩሃል። አንተ ፈቃዱን ታደርጋለህና። ትላከዋለህምና። ስለዚህ በፈርስህ አሰላለፍ እና በቀስትህ ሰገባ ነፀብራቅ ልባቸው ይንቀጠቀጣል። ከምድር ላይ ይሰግዱልሃል። ግርማህን በማየት ልባቸው ይደነግጣል። በተራራ ላይ ያሉም ሲያዩህ ወደ ምድር ይወርዳሉ በባህሮችና በቆላዎች ያሉትም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስላፈረሱ እግዚአብሔር በእጅህ ይጥላቸው ዘንድ ወደ ውጭ ይወጣሉ።

አንተ ግን ፈቃዱን በምታደርግ ጊዜ ከእሱ የለመንከውን ሁሉ ትቀበላለህ። ከወደድክ ይወድሃል። ትእዛዙንም ከጠበቅህ የልብህን ልመና ሁሉ ይሰጥሃል። የፈለከውን ሁሉ ከሱ ትቀበላለህ። ለቸሮች ቸር ለቅኖችም ቅን ነውና። ለሚፈሩት ፈቃዳቸውን ያደርጋልና። ለሚታገሱትም ዋጋቸውን ይሰጣቸዋልና። መኣትን ታገሳት። በኋላም ታስደስትሃለች። እውነትንም ውደዳት። ህይወትንም ታፈራልሃለች። ለቸሮች ቸር ለበዳዮችም ገሳጭ ነው።

ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን በእግዚአብሔር መንገድ ሄደው ብዙ በረከትን አገኙ። በውጭም በውስጥም የተከበሩ ነበሩ። ኢትዮጵያ የዳቦ ቅርጫት ነበረች። ሌሎች የሚማረኩበት የተፈጥሮ ውበት ነበራት። አኗኗራቸው ሌሎችን የሚማርክ ነበር። ኢትዮጵያ በከብቶች የተባረከች ነበረች። ወንዞቿ የሩቅ አገር ሰዎችን ሳይቀር ያለመልማሉ። ማርና ወተት የሞላባት አገር ነበረች። ከበረከቱ ብዛት የተነሳ አብርሃምና ይስኃቅ እንኳን ያላገኙት የመላእክት ዜማ ተለይቶ ለኢትዮጵያ ተሰጣት። የአዲስ ኪዳን ባለውል ኢትዮጵያ ድርሻዋ ይህ ነው።

ኢትዮጵያውያን ከእግዚአብሔር መንገድ ስንወጣ ደግሞ የሚደርስብን ቅስፈት እነሆ።

እርግማን ለኢትዮጵያዊው፥

ከአሕዛብ ሁሉ የጎደልክ ትሆናለህ።
በጠላትህ ድል ትነሳለህ።
ፊቱን ካንተ ይመልሳል።
ደንጋጣ፣ አዘንተኛና በልብህም ታማሚ ትሆናለህ።
መኝታህም ያለ ፀጥታና ጤና ይሆናል።
በዱር የተረገምክ ትሆናለህ።
በቤት የተረገምክ ትሆናለህ።
የምድርህ ፍሬ የተረገመ ይሆናል።
የሆድህ ፍሬ የከብትህና የበግህ መንጋ የተረገመ ይሆናል።
እግዚአብሔር ረሃብና በሺታ ይልክብሃል።
እስኪያጠፋህ ድረስ እጅህን ያሳረፍክበት ሁሉ ይጠፋል።
ቃሉን አልሰማህምና ሰማይ በራስህ ላይ መደብ በበታችህ ብረት ይሆንብሃል።
እግዚአብሔርም የምድርህን ዝናም ጭጋግ ያደርግብሃል። ከስማይም እስኪደፍንህ፣ በጠላትህ ፊት እስኪገድልህና እስኪያጠፋህ ድረስ ናዳ ይወርድብሃል።
በአንድ መንገድ ወደነሱ ትወጣለህ። በሰባት መንገድም ከነሱ ትሸሻለህ። የተበታተንክ ትሆናለህ። ስጋህንም የሰማይ ወፎች ይቀራመቱታል። የሚቀብርህም የለም።
በእከክና  ሺ በሚሆን ልዩ ልዩ ደዌና የወባ በሺታ፣ በግብፅ መቅሰፍቶች፣ በእውርነት በልብ ድንጋጤም ይቀስፍሃል። እውር በጨለማ እንደሚያደርገው በቀን እንደ እውር ትዳብሳለህ።
በግፍ ጊዜ የሚረዳህ የለም።
ሚስት ታገባለህ ሌላ ወንድም ይቀማሃል።
ቤትን ትሠራለህ በውስጡ ግን አትኖርም።
ወይን ትተክላለህ ፍሬውን ግን አትለቅምም።
የሰባውን በሬህን በፊትህ ያርዱታል። ከሱም አትበላም።
አህያህንም ይቀማሉ። አይመልሱልህምም። በጎችህ ለጠላቶችህ ይሆናሉ። የሚረዳህም አታገኝም።
ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለሌላ ህዝብ ይሆናሉ። ሲደበድቧቸው በአይኖችህ ታያለህ። የምታደርገው የለም።
የማታውቀው ጠላት የምድርህንና የድካምህን አዝመራ ይበላል።  መከልክልም አትችልም።
የተጨነቀና የደነገጠ ትሆናለህ። በየጠዋቱ እንዴት ይመሻል? ሲመሽም ከፍርሃት ብዛት የተነሳ እንዴት ይጠባል? ትላለህ።

እኛ ኢትዮጵያውያን ከእግዚአብሔር መንገድ ስለወጣን የደረሰብን ውድቀትና ውርደት ምን እንደሆነ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ አለን? ኢትዮጵያውያንን ያልቀሰፈ በሺታ አለን? በረሃብተኝነቷ ምክንያት ዓለም በኢትዮጵያ አልተሳለቀምን? የሰባውን የኢትዮጵያ በሬ፣ የሚያምረውን ቡናዋንም፣ የሚያጠግበውን እህሏንም፣ የሚያስጌጠውን ወርቋንም የውጭ አገር ሰዎች አንድ ዶላር ወይም አንድ ፓውንድ ወይም አንድ ፍራንክ ጥለው ሲወስዱት ኢትዮጵያውያን አይናችን እያየ አልተራብንምን? አይናችን እያየ አልታረዝንምን? አሁን ኢትዮጵያዊው አርሶ ወይም ሸምቶ ጎተራውን በጤፍ ወይም በስንዴ ወይም በማሺላ ሊሞላ ይችላልን? አሁን ኢትዮጵያዊው በግ አርዶ ሊመገብ ይችላልን? ወደ ውጭ አገር መሰደድን የማይሻ ኢትዮጵያዊስ አለን?

መጀመሪያ በረከቱ የተላለፈው በዳዊት ልጅ በኩል ነው። የእግዚአብሔርን ቃልኪዳን ይጠብቁ ዘንድ በመጀመሪያ የዳዊት ልጅ ከኢትዮጵያውያን ካጠገባቸው አለን? ኢትዮጵያዊው በአገሩ የተናቀ አይደለምን? ኢትዮጵያዊው በውጭ አገር የተናቀ አይደለምን? ምእራባዊው ኢትዮጵያዊውን አይንቅምን? ቻይናዊው ኢትዮጵያዊውን አይንቅምን? ቬትናማዊው ኢትዮጵያዊውን አይንቅምን? ህንዱ ኢትዮጵያዊውን አይንቅምን? ሜክሲካዊው ኢትዮጵያዊውን አይንቅምን? በውጭ አገር በባርነት የተገዙ ጥቁሮችን የሚንቁ አህዛብ ሁሉ ኢትዮጵያውያንን አይንቁምን? ኢትዮጵያዊው አልተዋረደምን?

ይህ ሁሉ ውድቀትና ውርደት ከደረሰብን በኋላ እግዚአብሔርን አላስታወስንም። በንስሐም ወደ እሱ ለመመለስ አልፈለግንም። ከንጉሥ እስከ ታናሺ፣ ከሊህቅ እስከ ደቂቅ፣ ከሊቀ ጳጳስ እስከ ምእመን ድረስ እኛ ኢትዮጵያውያን ለረጂም ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ አመጽን ቀጠልን። አባቶቻችን ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን ሻርን። ለእግዚአብሔር ሕግ አንገዛም፣ ሕግ አውጪዎች እኛ እራሳችን ነን ብለን የእግዚአብሔርን ጣልን። በዘመናት የተነሱ የኢትዮጵያ ነገሥታት የሩቅ አገር ፈረሰኞችን፣ ዝናራቸውን፣ አለባበሳቸውን፣ አቋቋምና ግርማቸውን በማየት ተማርከው የእግዚአብሔር የሆነውን እንቁውን በመዳብ ለመለወጥ ሴሰኑ። በጎችን ለተኩላዎች ለማቅረብ ድርድር ጀመሩ። በጎቻቸውን አስወጥተው ቤታቸውን ለጅብ ማደሪያ ሰጡ። የተቀደሰውን ለውሻ እንቁውንም ለእርያ አሳልፈው የሚሰጡ ጳጳሳትም በተለይ ከአምሳ አመታት ወዲህ እነሆ በቀሉ። ምንኩስናን በመሻት በረከትንና ምክርን እናገኛለን ብለው የተጠጓቸውን ልጃገረዶች በመድፈር የክርስቶስ ፍቅር የማረካቸውን ልጃገረዶች ከክርስትና የሚያስወጡ ሓሳዊ ካህናት እራሳቸውን አርክሰው አሁንም በተቀደሰው ቦታ ቆሙ፣ ቦታውንም አረከሱ። ካህናት በምእራባውያን ባህልና ፍልስፍና ተማረኩ። ምእመናንን እንደባቢሎን ሁኑ ብለው አስተማሩ። ከባቢሎን ሹማምንት ጋርም ተሰለፉ። በባቢሎን የዝሙት ወይን ጠጅ ሰከሩ። ወንድማማቾች በአንድ ላይ እግዚአብሔርን እንዳያመሰግኑ ከዓለም አማጽያን፣ ከባቢሎንና ከእስማኤላውያን ጋር በማበር ኢትዮጵያውያንን ከፈሉ። ለአይሁድ ነን ባዮችና ለባቢሎን ሹማምንት በር በመክፈት የክርስቶስን ምእመናን ለአራዊት አጋልጠው ክርስቶስን አስክደው ወደ አይሁድነት ነዱ።  ጥንት ምህላና ጥዑም የምስጋና  ዜማ በባጀበት አሁን የሚነጥቁ፣ የሚሴስኑና የሚደልሉ ተኩላዎች የክህነት ልብስ ለብሰው ነገዱበት። በጎችንም በተኗቸው። የተበተኑትንም የባቢሎን ፈረሰኞች ማርከው ወሰዷቸው። ውሾችና እርያዎችም ከኢትዮጵያውያን የቀረበላቸውን የተቀደሰውንና እንቁውን ረገጡ። ተመልሰውም ኢትዮጵያን ነከሱ። 

እኛ የኢትዮጵያ መሃይምናንም የባቢሎንን ዋንጫ አነሳን። የባቢሎንን ወይን ጠጅ ተጎነጨን። በባቢሎንም የወይን ጠጅ ሰከርን። እነሆ በስካር ላይ ነንና በምድር ላይ ካሉ ሰዎች ሁሉ በታች እንደዋልን አናውቅም።

ይህን የባቢሎንን ወይን ጠጅ የጠጣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሙያው ክፋት፣ አንደበቱ ትእቢት፣ ባህሉም ምቀኝነት ሆነ።
አሁን ኢትዮጵያዊው ከተፈጨ በርበሬ ውስጥ የተፈጨ ቀይ ሸክላ፣ ከምግብ ዘይት ውስጥ የሞተር ዘይት፣ ከጠጅ ውስጥ ስሚንቶ፣ ከጤፍ ውስጥ አሸዋ እየጨመረ በመሸጥ እህትና ወንድሞቹን ባለደዌ አድርጎ እርሱ መበልጸግን የሚሻ ክፉ ሆኗል።

አሁን ኢትዮጵያዊው ያገሩን፣ የወንዙን  ልጅ፣ ኮረዳዋን ልጃገረድ የትዳርና ልጅ የመውለጃ እድሜዋ እስከሚያልፍ ድረስ የሚወድ መስሎ ያለትዳር ለረጂም ጊዜ  መጠቀሚያ በማድረግ የትዳር እድሜዋ ካለፈ በኋላ ፈላጊ ከሌለበት ምድረበዳ ላይ ጥሏት የሚሄድ ክፉ ሆኗል።

አባት፣ እናት፣ ልጅ፣ ጎረቤት፣ ዘመድ፣ ሠፈርተኛው፣ የከተማው ሰው፥ በጠቅላላ እኛ ኢትዮጵያውያን አንድም ሳይቀር አገራችን በጥድፊያ የመስረቅ ዘመቻ ላይ ተሠማርተናል። አሁን የእኛ የኢትዮጵያውያን ጨዋታችን፣ ምሳሌያችን፣   ምክራችን፣ እቅዳችንና ስምሪታችን ሁሉ፡ ስለ ስርቆትና  በቅጥፈት ስለመክበር ሆኗል። በዚህ በስርቆት ምክንያት የቀረው ኢትዮጵያዊ ይራባል፣ ይጠማል፣ ይሞታል ብሎ ቅር የሚሰኝ አንድም አይገኝም። 

በአዋጅ፣ በቃል ኪዳን፣ የዳዊት መንበር ሆና  ኢትዮጵያ ለክርስቶስ ከታጨች ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ አመታት በኋላ ኢትዮጵያውያን የጣኦት አምላኪዎች ሆነናል። ለሰይጣን አመት በዓል ሰይመን በሃይቅ ለስይጣን እንሰግዳለን፣ ለስይጣን እነሰዋለን፣ ለስይጣን ዳንኪራ እንመታለን።

ከተኹሎች ጋር በተኹሎች ገበታ የበግ ወጥ ለመብላት በግ ትቀርባለችን? አሁን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ኢትዮጵያውያንን ሊያጠፉ የሚሹትን ሰዎች ቋንቋ እየተናገሩ የጥፋቱን እርሾ ለአጥፊዎቹ አዘጋጅተዋል።

እኛ ኢትዮጵያውያን በቤታችን ግፍና ጭካኔ፣ በመንገድ ሌብነት፣ በማህበር ቅጥፈት፣ በልባቸን በእግዚአብሔር ላይ አመጽ፣ በቤተክርስቲያን ክህደት፣ በውጭ አገር ፍልስፍና ተስፋ፣ የእጅ ሥራ ውጤቶችንም እንደ አምላክ  አድርገናልና፣  ይህም እግዚአብሔርን አስቆጥቷልና፥ እነሆ አለንጋ መጥቷል።

ማንበብ የምትችሉ አንብቡ ላላነበቡም በሚገባቸው ቋንቋ ተናገሩ። ጆሮ ያላችሁ ስሙ ላልሰሙም አሰሙ። ከነነዌ ሰዎች እንማር። በኢትዮጵያ እሳት እንደ በረዶ ይዘንባል፣ የእሳት አሎሎ ክጸሐይ ይወረወራል።  ዝናብ ዘንቦ መሬት በበረከት ጭቃ መጨቅየቷ ይቀራል፤ እሳት ወርዶ በተቃጠለ የነዳጅ አተላ እንደጨቀየች ትሆናለች። የኛ የኢትዮጵያውያን አመጽና ርኩሰት ጌታችን እግዚአብሔርን አስቆጥቷልና።  እኛ ኢትዮጵያውያን በእግዚአብሔር ላይ የፈጸምነው በደል ቁጥር ስፍር የለውምና። ትእዛዙም በቀጥታ ከእግዚአብሔር ነውና። በመአቱ እሳት እንዳንቃጠል እንደ ነነዌ ሰዎች ከሽማግሌ እስከ ህጻን ድረስ እንጹም፣ እናልቅስ፣ እንጸልይ። ከክፉ ሥራችን እንታቀብ። ለንስሐ እንምከር። የጋራ ንስሐም ቀነ ቀጠሮ እናዘጋጅ። ማን ያውቃል፥ ከልባችን ተጸጽተን ንስሐ ከገባን እግዚአብሔር እንደ ነነዌ ሰዎች ይቅርታ ያደርግልን ይሆናል።

ከላይ ከተመለከተው ተጨማሪ በድንግል ማርያም ላይ ለዘመቱ እነሆ።

ይህን ያነበበ ወይም የሰማ ላልሰማው ያሰማ። በእሳት እንዳይበላ። እሳት ወደ ሁሉም ይመጣል የሚያተርፈውን እሱ እግዚአብሔር ያውቃል። ደግሞም በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ እጣቱን የቀሰረ ወይም በቅድስቷ ላይ ክፉን ያሰበ ወይም በሷ ላይ በስንፍና የተናገረ ኢትዮጵያዊ ግድግዳ ካጠገቡ ካለ ግድግዳው አፉን ከፍቶ ያላምጠዋል። በመሬትም ላይ ከቆመ መሬት አፏን ከፍታ ትውጠዋለች። እጣ ፈንታው ይህ ነውና። ያልሰማ ይሰማ ለሌላውም ያሰማ። ይጠንቀቅም። 


ለነነዌ ይቅርታን ያደረገ አምላክ ኢትዮጵያንም በይቅርታ ይጎብኛት። የዚህ መልእክት ውጤትም እንደ ዮናስ ወልደ አማቴ መልእክት ይሁን። አሜን።

መስከረም ፲፪ ቀን ፪፲፻፬ ዓ.ም.

ሙሉጌታማሳሰቢያ፣ ማስጠንቀቂያ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ።

 HOME