ከባቢሎን ውጡ

ስለ ምዕራቡ ዓለም የመጨረሻ ዘመናት ቅዱስ መጽሐፍ ምን ይላል?

ኅጥእን ከፍ ከፍ ብሎ፣ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት። ስመለስ ግን አጣሁት።

በአይኖቹ መካከል ትልቅ ቀንድ ያለው አውራ ፍየል መሬት ሳይነካ ምድርን ሁሉ እያቋረጠ በድንገት ከምዕራብ መጣ፤ በወንዙ አጠገብ ቆሞ ወዳየሁት፣ ሁለት ቀንድ ወዳለው አውራ በግ ተንደርድሮ መጣበት። በታላቅ ቁጣም መታው። እየወጋውና ሁለቱን ቀንዶቹን እየሰበረ፣ በጭካኔ አውራውን በግ ሲጎዳ አየሁ፣ አውራ በጉም ለመቋቋም ጉልበት አልነበረውም። ፍየሉ በምድር ላይ ጥሎ ረገጠው፣ አውራ በጉንም ከፍየሉ ለማዳን የሚችል አልነበረም።  ፍየሉም ታላቅ ሆነ፣ ነገር ግን በኃይሉ በበረታ ጊዜ ትልቁ ቀንዱ ተሰበረ፣ በቦታውም ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት የሚያመለክቱ አራት ታላላቅ ቀንዶች በቀሉ። ከነዚህም ቀንዶች መካከል ከአንዱ ላይ አንድ ሌላ ትንሽ ቀንድ በቀለ፣ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምስራቅና ወደ መልካሚቱ ምድር በኃይል አደገ። ወደሰማይ ሰራዊት እስኪደርስ ድረስ አደገ። ከከዋከብት ሠራዊትም የተወሰኑትን ወደምድር ጣለ፣ ረገጣቸውም። ከሰማይ ሰራዊት አለቃ ጋር እስኪስተካከል ድረስ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፣ የልዑልንም የዘወትር መስዋእት ወሰደበት። የመቅደሱንም ስፍራ አረከሰ። ከአመጽ የተነሳም የቅዱሳን ሰራዊት ከዘወትሩ መስዋእት ጋር ለሱ አልፎ ተሰጠ። የሚያደርገው ሁሉ ተከናወነለት። እውነትም ወደምድር ተጣለች።

ቅዱስ ገብርኤልም ለነቢዩ ዳንኤል እንደዚህ ብሎ ተረጎመለት፦

አውራው ፍየል የግሪክ መንግስት ነው። በአይኑ መካከል ያለው ታላቁ ቀንድም የመጀመሪያው  ንጉሥ ነው። ይህ ንጉስ ያልፍና በምትኩ አራት መንግስታት ይነሳሉ። በዘመነ መንግሥታቸው በስተመጨረሻ፣ አመጸኞች ፍጹም እየከፉ በሄዱበት ጊዜ፣ አስፈሪ ፊት ያለው ገዢ ይነሳል። የራሱ ፍልስፍናም ይኖረዋል። የእግዚአብሔርንም ይጥላል። በሳይንስና በእደ ጥበብ ይበለጽጋል። መሬትን ያበላሻል፣ በሰላምና በፍትህ ስም ብዙዎችን ይደመስሳል።

የምዕራባውያን ብልጽግና ከአመጽ አበቃቀሉ

የምዕራብ ሰዎች በአማርኛ ሲተረጎም "እንደገና በሰው መንገድ መወለድ" በሚባለው፣ በምዕራባውያን ቋንቋ ደግሞ ሬናሰንስ (Renaissance) ተብሎ በሚጠራው፣ ከጣሊያን አገር፣ ከሎሬንስ ከተማ፣ በምዕራባውያን አቆጣጠር፣ በአስራ አራተኛው ምእተ ዓመት በፈለቀ የአስተሳሰብ ጎዳና ተጉዘው አሁን ያሉበት ቦታ ደርሰዋል። ጎዳናው የሰው ጎዳና ነው፣ የደረሱበት ሰፈርም የሰው ፍላጎት ሰፈር ነው። ሬናሰንስ ምንድን ነው?
የሬናሰንስ አምጭዎች አውሮፓ በኦርቶዶክስና በካቶሊክ እምነቶች በሚጓዝበት ዘመን፤ የሰው ፍላጎት በክርስትና ህጎች ታስሯልና፣ ከዚህ ከክርስትና እስር ቤት ተላቅቀን አካላዊ ደስታ በሚገኝበት መንገድ መጓዝ አለብን የሚል አስተሳሰብ አፈለቁ። የዚህ አስተሳሰብ አባት የሚባለው ኢጣሊያዊው ፍራንሴስኮ ፔትራች አንድ ጊዜ በደቡብ ፈረንሳይ ውስጥ የሚገኜውን ቬንቱ የተባለውን ተራራ ከወጣ በኋላ የአዲሱን ፍልስፍናውን ጽንሰ ሃሳብ ለማስተዋወቅ "እኔ ይህን ተራራ የወጣሁት በራሴ ችሎታ ነው። የምኮራውም በራሴ ነው። ክንዋኔውም የራሴ ነው አለ። ሁሉም ነገር የሚደረገው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው የሚለውን፣ ቀደም ሲል የነበረውን የአስተሳሰብ መንገድ በመጻረር ነበር ይህን አስተያየት የጻፈው። የእሱንም ፈለግ ተከትለው ብዙዎቹ ከኃይማኖት ተጽእኖ ነጻ መውጣት አለብን እያሉ አስተጋቡ። በስነ ግንባታ፣ በስነ ጽሁፍ፣ በስነ ሰእል እና በሌሎችም ሥራዎች የሰውን አካላዊ ስሜት የሚቀሰቅሱ፣ የእግዚአብሔርን ውደሳ የሚቀንሱ ሥራዎችን ማስፋፋት ጀመሩ። ይህ አዲስ አስተሳሰብ ከጣሊያን ወጥቶ ወደሌሎቹ የአውሮፓ አገሮች እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጠለ። የሰውን አካል በደስታ ለማርካት የታለሙ ብዙ የእጅ ሥራዎች፣ ስነ ጽሁፎች እና የሳይንስ የምርምር ሥራዎች ተስፋፉ። ብዙዎቹ አውሮፓውያን ፈላስፎች የክርስትና ኃይማኖት የአካላዊ ደስታና ብልጽግናን ለማግኜት ወደፊት እንዳንገፋ አግዶናል እያሉ ክርስትናን ተቃወሙ። አንዳንዶቹ ደግሞ ክርስትናን ከአዲሱ አስተሳሰብ ጋር አብሮ ማራመድ ይቻላል አሉ። እንዲያውም ክርስትና አዲሱን አስተሳሰብ እንዲያገለግል ማድረግ ይቻላል የሚል አስተያየት አንዳንዶቹ ያዙ። በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በአዲሱ እምነት በመገፋፋት ማርቲን ሉተር የሚባል አንድ ጀርመናዊ ሰው ከካቶሊካዊ እምነት ወጥቶ የካቶሊክን አመራር በመቃወም "ሰው በእምነት እንጂ በስራ አይድንም፤ ክርስትናም በመንግስት ስር መዋል አለበት" የሚል ሃሳብ አቀረበ።   አስራ ሁለት መነኮሳትን ከገዳም አስኮብልሎ በማስወጣት ወደ ስጋዊ ደስታ ሰፈር ያስገባው ማርቲን ሉተር፣ መጽሐፍ ቅዱስንም በራሱ መንገድ ወደ ጀርመንኛ፣ ስድስት ጥራዝ፣ ስልሳ ስድስት መጽሐፍ አድርጎ ተረጎመው። አውሮፓም ተቀበለው። ስድስት ጥራዝ፣ ስልሳ ስድስት መጽሐፍ ያዘለውንም የማርቲን ሉተር ትርጉም እውነተኛው መጽሐፍ ይህ ብቻ ነው አሉት። ነጻ ወጣንም አሉ። ሰው የሚጸድቀው በእምነት ብቻ ነው የሚለው አዲስ አስተሳሰብ አካላዊ ደስታን ላማሳደድ እጅግ ተስማሚ መሆኑን አውሮፓውያን ወደዱ።

 HOME

ከላይ እንደምናየው የአውሮፓ ብልጽግና ነቢዩ ዳንኤል በትንቢት የተናገረው፣ ቅዱስ ገብርኤል የተረጎመለት የአመጽ ብልጽግና መሆኑን ማስተዋል ይጠቅማል። ቅዱስ ገብርኤል ለዳንኤል እንደገለጸለትም በቅዱሳን ላይ ለጊዜው የበላይነትን ያሳዩ እንጂ በመጨረሻ የበላይነት የሚኖራቸው የተገፉ ቅዱሳን ናቸው። የኢትዮጵያ ሰዎች የአውሮፓን ብልጽግና አይተው፣ የእምነቱ ፍልስፍናም ማርኳቸው ቢጠለፉ በመጨረሻ እጥፍ ድርብ ጊዜ ይጎዳሉ። 
ከጀርመን ነገድ በፈለሱ ሰዎች ሰፋሪነት በአገርነት ለመደራጀት ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት ዓመት የወሰደባት እንግሊዝ፣ በተለይ የሬናሰንስ አካል በሆነው በፕሮቴስታንት አስተሳሰብ ብዙ አትርፋለች።  በቅኝ ገዢነት ለመስፋፋት ወደ ደቡብ፣ ወደ ምስራቅና ወደ መልካሚቱ ምድር በኃይል እንዴት እንዳደገች የሚዘነጋ አይደለም። የምዕራቡ፣ በተለይም የእንግሊዝ ፈላስፋዎችና፣ የሳይንስ ጠበብቶቿ ከሰማይ ሰራዊት አለቃ ጋር እስኪስተካከሉ ድረስ ራሳቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ። ቻርለስ ዳርዊንና መሰሎቹ የራሳቸውን ኦሪት ዘፍጥረት ከእንግሊዝ አገር ተረኩ። ቢቻላቸው በሳይንሳቸው ቅዱሳንን እስኪያስቱ ድረስ አከናወኑም።

በተለይ በእንግሊዝ የፕሮቴስታንት አብዮት የጌታችን የመዳህኒታችን እናት ብጽእት የቅድስት ድንግል ማርያም ስም በብዙ መንገድ ተሰደበ። ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ቦታ ከማንኛውም ቦታ በተለየ መንገድ የተጠላችበት ቦታ ነበር። የአዲሱ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ስእሏን እያሳደዱ አቃጠሉ። ስሟ እንዳይጠራ ዘመቱ። በዚህ ጊዜ ዋልሲንግሃም በተባለ ቦታ፣ በፕሮተስታንቶች ይሳደዱ የነበሩ ሰዎች የጻፉት ግጥም በመጠኑ በአማርኛ ተተርጉሞ ከዚህ በታች ለታሪክ መዘክር ይሆን ዘንድ እነሆ፦

ደህና ሁኝ ዋልሲንግሀም፣
አንች ሰፈረ መርገም።
ገነት ገሀነም ሊሆን ባንቺ ኃጢያት ተሠራ።
በአሳዳጆች ሲሰባበር የእመቤታችን ክብሯ።

ወደ ሰማይ  የሚያሳዩት ዋልታዎችሽ ተጋደሙ፣
ከመሬት ጋር ተላተሙ ።
መግቢያ በር እንዳልነበረ፣
በማይታወቅ ጎዳና ጠፍቶ ቀረ።

መዝሙርስ  የት ገባ?
በሚጣፍጠው ዜማ ሰፈር፣
ጭላቶች ያቅራሩበት ጀመር።

ባለ ዘንባቦች ሆሳእና ባሉበት፣
ዘንዶና እንቁራሪት መሸጉበት።

ወዮልሽ ዋልሲንግሃም፣
ዋይ ዋይ ብለሽ አልቅሺ፣
ቀኖችሽ ጨልመዋልና፣
በረከትሽ ተረግሟልና፣
ቅድስናሽ ረክሷልና።

እመቤታችን በቆየችበት፣
ኃጢአት መቶ ነገሰበት።
ጌታችን ባዘዘበት፣
ሰይጣን መቶ ሰፈረበት።
ደህና ሁኚ ዋልሲንግሃም፣
አንቺ ሠፈረ መርገም።

የሉተርና የካልቪን መንገዶች ከአውሮፓ ወጥተው፣ ባህር አቋርጠው፣ ብዙ እልፍ የሚሆኑ ሰዎችን ከኢየሩሳሌም እንዲሰደዱ አድርገዋል። አሁን የሉተርና የካልቪን የፕሮቴስታንት ኃይማኖት ድርጅቶች ቁጥር ከሰላሳ ሶስት ሺህ አልፏል። ሁሉም በየፊናቸው በዓለሟ ዙሪያ፣ አንድ ጊዜ በጎዳና፣ አንድ ጊዜ ባደባባይ፣ በማእዘኑም ሁሉ ተሠማርተው ብላቴናዎችን "ኢየሱስ ከኛ ዘንድ አለና መጥተህ እንደግል አዳኝህ ተቀበል" በሚል ማባበያ፣ በከንፈራቸው ልዝብነትና በብዙ ጨዋታ የዋሆችን ከኢየሩሳሌም በመጎተት ላይ ናቸው። አንዷን የብርሃን መንገድ ተዋህዶን ጨለማ ብለው ስም አወጡላት፤ ብላቴናዎችን ኑ በተወደደ መተቃቀፍ ደስ ይበለን እያሉም ሰበሰቡ። በሬ ለመታረድ እንዲነዳ፣ ውሻም ወደ እስራት እንዲሄድ፣ ወፍ ወደ ወጥመድ እንደሚቸኩል፣ ለነፍሳቸው ጥፋት እንደሆነ ሳያውቁ፣ ብርሃን ነው እያሉ በዚህ የሉተር የጨለማ መንገድ ብዙ፣ እጅግ ብዙ ብላቴናዎች ጠፉ።

የአመጽ ፍሬ መልካም ሊሆን ይችላልን? ምንም አይነት ስም ይኑረው ምንም ከሉተርና ከካልቪን ትምህርቶች ተዋርዶ የመጣ ማንኛውም እምነት ምን ጊዜም የአመጽ ነው። ታሪኩ በየትኛውም መጽሐፍ ከላይ እንደተገለጸው ነው። ከክፉ ዛፍ ምንም ቢሆን ምን መልካም ፍሬ አይገኝምና በነዚህ እምነቶች የተጠለፉ የኢትዮጵያ ሰዎች ከባቢሎን የሚወጡበት ጊዜ አሁን ነው። መዘግየት መሞት የሚሆነው እዚህ ላይ ነው። 

የምዕራብ ሰዎች ክርስትናን "አካላዊ ደስታን ማግኜት" ለሚለው ለአዲሱ አስተሳሰብ መገልገያ እንዴት እንዳዋሉት ምንም ትንታኔ ሳያስፈልግ የሚከተለውን ደብዳቤ በማንበብ ማረጋገጥ ይቻላል።

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1883 ዓ.ም. ከቤልጂየሙ ንጉሥ ከሊዮፖልድ ሁለተኛ  በኮንጎ ለተሰማሩ ለቤልጂየም ሚሺነሪዎች  የተላከ ደብዳቤ እነሆ፦

ብጹአን፣ ለአባቶችና ለውድ ወገኖች፦

እንደትወጡ የተሰጣችሁ ብዙ መላን የሚጠይቅ፣ ጥንቃቄን የሚሻ ሃላፊነት ነው። በርግጥ ወንጌልን ልታስተምሩ ነው የምትሄዱት፤ ነገር ግን ከሁሉም በላይ ወንጌሉ የቤልጂየምን የሀገር ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆን ይኖርበታል። በኮንጎ ዋናው አላማችሁ ጥቁሮች እግዚአብሔርን እንዲያውቁት ማድረግ አይደለም። እግዚአብሔርን አስቀድመው ኣራሳቸው ያውቁታል።  ሙንጉ፣ ንዛምቢ እና አንድ ንዛኮምባ ስለሚባል ይናገራሉ። ሌላ እንዳለም አላውቅም። ሰውን መግደል፣ ከሌላ ሰው ሚስት ጋር መተኛት፣ መዋሸትና መሳደብ መጥፎ እንደሆኑ ያውቃሉ። የሚያውቁትን ነገር ልታስተምሯቸው እንደማትችሉ ልቦናችሁ ይወቅ። ዋናው አላማችሁ እኛ የምንልካቸውን አስተዳዳሪዎች ሥራ ምቹ ማድረግና ሥራችሁ ወንጌሉ በአላችሁበት የዓለም ሠፈር ጥቅማችሁን እንዲያስጠብቅ ማድረግ ነው። ይህ ዓላማ እንዲሳካም እነዚህ ኋላ ቀሮች ከሚኖሩበት ምድር ያለውን የማያልቅ የተፈጥሮ ሃብት እንዳያስተውሉት ከማድረግ አትቦዝኑ። ከመሬታቸው በታች ያለውን ሃብት ያወቁ እለት በአመጽ ይገለብጧችኋልና እንዳያውቁት አድርጉ። 

በወንጌል ያላችሁን እውቀት ተጠቅማችሁ ከወንጌሉ ውስጥ አንዳንድ ልትጠቀሙባቸው የምትችሉ ስንኞች አታጡምና እንሱን በመጥቀስ ድህነትን እንዲወዱ አድርጓቸው። ለምሳሌ "ደሆች ደስተኞች ናቸው ምክንያቱም መንግሥተ ሰማይን ይወርሳሉና" የሚለውንና "ኃብታም መንገሥተ ሰማያት ለመግባት ያዳግተዋል" የሚሉ ስንኞችን በስልት እየተረጎማችሁ እንዳያድጉ አድርጓቸው።  ካጠገባቸው አትኑሩ፣ እኛን የሚቃወሙ ምግባሮችን እንዲጠሉ አድርጓቸው። በተለይ ይህን የውጊያ ስልታቸውን ሊተው የሚፈልጉ አይመስሉምና ያላችሁን ችሎታ ተጠቅማችሁ እንዲተውት አድርጓቸው።

በተለይም በወጣቶች ላይ  አተኩሩ። የወንጌል አስተማሪዎቻቸው የሚያስተምሯቸውን  የሚጻረር አመጽን ከማድረግ ይቆጠባሉና። ልጆቹ ለሚሽነሪዎች መታዘዝን መማር አለባቸው። ከሁሉም በላይ መላ ሰውነታቸው ለኛ እንዲታዘዝ ማድረግ ዋና አትኩሮታችሁ ይሁን። በትምህርት ቤት የእድገትን ሚስጢር አይወቁ። እንዲያነቡ እንጂ እንዲያስቡ አታድርጓቸው። ይህን ለማከናወን የሚረዷችሁ ብዙ መጻህፍቶች አሉ፣ ይሰጧችኋል። ጥቁሮች ለነጮች የዘላለም ታዛዢ እንዲሆኑ  ለማድረግ በሚያስችል መንገድ ወንጌልን አስተምሩ። ዘወትር "የሚያለቅሱ ደስተኞች ናቸው፣ የእግዚአብሔር መንግሥት የነሱ ናትና" እያላችሁ አነብንቡ።

ጥቁሮችን የምትቀይሩት አለንጋውን በመጠቀም ይሁን። ሴቶቻቸው ለዘጠኝ ወራት በፍጹም ታዛዢነት እንዲያገለግሉን አድርጉ። ለእናንተ ታዛዢነታቸውን የሚገልጹበት ፍየል፣ ዶሮና እንቁላል መንደራቸውን በጎበኛችሁ ቁጥር እንዲሰጧችሁ አድርጉ። የትኛውም ጥቁር ሃብት እንዳይኖረው አድርጉ። በየቀኑ ሃብታሞች መንግሥተ ሰማያት አይገቡም እያላችሁ ዘምሩ። ግብር በየሳምንቱ እሁድ እንዲከፍሏችሁ አድርጉ። ከነሱ ያገኛችሁትን ገንዘብ የንግድ ተቋሞችን ስሩባቸው። ኃጢአታቸውን የሚናዘዙበት ቦታ አዘጋጁና የሚያስቡትን ተከታተሉ። ጥቁሮች ጀግኖቻቸውን እንዲረሱ፣ የኛን ጀግኖች ብቻ እንዲወዱ አድርጉ። ጥቁር ሊጎበኛችሁ ከመጣ በፍጹም ወንበር አታቅርቡለት። ከአንድ ሲጋራ በላይ አትስጡት። ምንም ያህል በጎበኛችሁት ቁጥር ዶሮ ቢሰጣችሁም ጥቁርን በፍጹም እራት አትጋብዙት።

ኪሊዮፖልድ ሁለተኛ
የቤልጂየም ንጉሥ
   
እንግዲህ እነሆ የምዕራቡን ክርስትና አስተውሉ። ኢየሩሳሌም ተዋህዶን ትቶ ወደምዕራቡ እምነት መሰደድ ሁለት ጊዜ መሞት እንደሆነ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ሰው ይወቅ። እውነተኛዋ መንገድ በኢትዮጵያ ያለችው መሆኗን ማዎቅ ለሁሉም ይጠቅማል። ወደእግዚአብሔር ዙፋን መድረስ የሚቻለው በሷ መንገድ ሲሄዱ በመሆኑ በመንገዷ ለመጓዝ ጥበብን ከልብ ማንቃት ያስፈልጋል።

ደክማ ሆና ከጉልበተኞች ይልቅ ትፈራለች፤ ከዓለም የተሻለን ፀጋ ይዛ ከእግዚአብሔር በራቀች ዘመን ዓለም እስኪያተኩር ድረስ ትቸገራለች፤ ህዝቦቿ ወደ እግዚአብሔር በቀረቡ ዘመን የሷ ጥቂቱ ብዙ ካላቸው ይልቅ ይበረክታል። ኢትዮጵያ እንቆቅልሽ ናት።

ክርስቶስን የሚያመሰግኑ ሌዋውያን አሁን በቴላቪቭ የሉም። በመሬት ላይ ያለች የምስጋና ምድር ኢትዮጵያ ናት። እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እንድናመሰግነው የመላእክትን ዜማ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ከሁሉም ለይቶ ሰጥቷል። እግዚአብሔር መልእክቱን ለኛ የነገረበት ቋንቋ ይህ ነው። ኢትዮጵያውያን የእግዚአብሔርን ህግ እንዲጠብቁና ከሥርአቱም እንዳይወጡ በተለያየ መንገድ እግዚአብሔር ተናግሯል። የእግዚአብሔርን መንገድ ብንከተል በረከትን፤ ከመንገዱ ብንወጣ ፍርድን እናገኛለን። ምዕራባውያን ብዙ ወርቅና አልማዝ አላቸው፣ ህንጻዎቻቸው ያምራሉ፣ ፍልስፍናቸውም ይማርካል ብለን ኃይማኖታችን ከነሱ ኃይማኖት ጋር ለማመሳሰል ብንሻ እንወድቃለን፣ እንዋረድማለን። ባለፉት አመታት በኢትዮጵያውያን የተፈጸመው ፍርድ ከዚህ የመነጨ ነው። እስራኤላውያን ግብጽ የሰለጠነ ነው ብለው የእግዚአብሔርን መና ለመናቅ መሻታቸው ምሳሌነቱ ለኛ እንደሆነ አንዘንጋ። ወደፊታችን የእግዚአብሔርን መንገድ ለመከተል ከልባችን ጥበብን እናንቃ፣ ከአባቶቻችን ያገኘነው ከእንቁና ከምድራዊ ፍልስፍና ሁሉ የከበረ ፀጋ እሱ ነውና።

የኢትዮጵያ የሥራ ድርሻ እግዚአብሔርን ማመስገን ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በማለዳ፣ በቀትር፣ በምሽት፣ በሌሊት፣ በሥራው፣ በውጤቱ፣ በሚያገኜው ምርት፣ በሰላምታው፣ በትህትናው፣ በእርምጃው፣ በአለባበሱ፣ በጌጡ ሁሉ ሳይቀር እግዚአብሔርን ማመስገን ይኖርበታል። ይህ የሆነ ቀን እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ቃል እንደገባው፣ ልጆቿ ሁሉ በመንገዳቸው የተባረኩ ይሆናሉ፣ ቤታቸውም፣ በራቸውም ይባረካል። የሆዳቸው ፍሬ ይባረካል፣ የምድራቸው ፍሬ ይባረካል፣ ወንዞቿ እንደገና ይፈሳሉ፣ ደኖቿ ይለመልማሉ፣ የተክሎቿ ፍሬዎች ይባረካሉ፣ በረቶቿን ከብቶችና በጎች ይሞሉታል፣ ይባረኩማል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ያከማቸውን በረከት ይጎበኘዋል፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በአገሩ ይከበራል፣ በውጭም ይከበራል፣ ኢትዮጵያን የሚቃወሙ ከእግሮቿ በታች ይወድቃሉ፣  በእያንዳንዱ ቤት በረከት ይሞላል፣ ከብቶቿ ይረባሉ፣ የኢትዮጵያዊ እድሜ ረጂም ይሆናል፣ ኢትዮጵያ ለሌሎች ታበድራለች እሷ ግን አትበደርም። ኢትዮጵያዊ ራስ ይሆናል እንጂ ጅራት አይሆንም፣ የኢትዮጵያ ክብር እንደ ብርሃን በዓለም በሚኖሩ ህዝቦች፣ በወገኖቿም ላይ እንደ ንጋት ኮኮብ ያበራል። ኢትዮጵያ ጠላት የሆኗትን ትወርሳለች፣ የሚጠሏት የማረኩባትን ህዝቦቿን፣ ቆላዎቿን እና ባህሮቿንም  በመንቀጥቀጥ ይለቁላታል። 

ይህ እንዲሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እናድርግ፣ ትእዛዙንም እንጠብቅ። ወንድሙን በክፉ የሚበድልን እንቆጣ፣ ክፉውን ከክፋት እናስወግድ፣ አድሎና ማማለጃን እንተው፣ በጠላት፣ በወዳጅ፣ በባለጸጋና በደሃ ፊት ፍርድ እንዳይጓደል እውነትን በትጋት እንሻት።

የእግዚአብሔር ስም ይቀደስ


ሃንስ ሆልቤንስ የተባለው ሰው በ1538 ዓ.ም. "የሞት ዳንስ" በሚባለው ስእሉ የፕሮቴስታንት እምነት መነኮሳትን ከገዳማት ማስኮብለሉን የገለጸበት ስእል

በዚህ አስተሳሰብ በመደገፍ ነበር ምዕራባውያን በቸገራቸው ዘመን የሌሎችን ሰዎች አገሮች በወረራ ይዘን አካላዊ ደስታን ማግኜት እንችላለን ብለው የተነሳሱት። በኢየሱስ ክርስቶስ እስካመንን ድረስ በግብር ደስታን በማሳደዳችን በመንፈስ አንጎዳም ብለው ልዩ ልዩ አገሮችን በቅኝ ግዛትነት መያዝ ጀመሩ። ይህም ለስጋ ተስማሚ በመሆኑ ምክንያት የፕሮቴስታንት እምነት አውሮፓን በሙሉ ማረከ። አውሮፓ ወደ ፕሮቴስታንት እምነት ማዘንበሉ የካቶሊክ እምነት ማእከልን ስላሳሰበ የካቶሊክ ማእከልም በበኩሉ ለአውሮፓ ተስማሚ የሆኑ ማስተካከያዎችን አደረገ። የሰው አገር በቅኝ ግዛት መያዝ በካቶሊክም የሚፈቀድ ሆነ። ካቶሊኮች ጀስዊት የሚባል ቡድን በማቋቋም የፕሮቴስታንትን ግፊት ለመፎካከር፣ ቢቻልም ለመግታት ተነሳሱ። ካቶሊኮች ግን በቅኝ ግዛት የሚይዙትን ወደ ካቶሊክ እምነት መቀየር እንደ ዓላማ አድርገው ያዙት።