በጽሁፍ የቆየው ታሪካችን እንደሚያስተምረን ኢትዮጵያ ወርደ ሰፊ ነበረች። አሁን ሶማሊያ፣ ጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ የመን እየተባሉ የሚጠሩት ቦታዎች የኢትዮጵያ አካሎች ነበሩ። አባቶቻችን ይህን ታሪክ በመዝገብ አቆይተውልናል። አባቶቻችን ይህን ሲነግሩን እነሱ በሚፈልጉት መንገድ እንድናስብ የረቀቁ ትምህርቶችን የሚነድፉልን፣ አባቶቻችሁን አትስሟቸው፣ ውሸታሞች ናቸው፤ የሚሉን ምእራባውያን ደግሞ እንኳን በእነዚህ የኢትዮጵያ አካል በነበሩ ቦታዎች የሚገኙ ሰዎች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ናቸው ብለን እንድናስብ ቀርቶ ደሴ እንኳን ኢትዮጵያ የነበረ አይምሰላችሁ ይሉናል። ደሴ ሲሉ ደሴ እንጅ እንኳን ኢትዮጵያን ወሎንም አይጨምርም ይሉናል። ጎንደር ሲሉም፣ ጎንደር ብቻውን ነበር እንጂ እንኳን ኢትዮጵያን በጌምድርንም አይጨምርም ይሉናል።  አክሱም ሲሉም አክሱምን ብቻ እንጂ፣ እንኳን ኢትዮጵያን ትግራይንም በታሪክ አይጨምርም ይሉናል። ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ሰው አማኝ ስለሆኑ ፈረንጅ የሚለውን እንደራሳቸው እየመሰላቸው በደግነት ስለሚቀበሉ ነው እንጂ ትኩር ብለው ቢያዳምጡ ያለባቸውን ስድብ ማንም ሰሚ እንደማይችለው ያውቁ ነበር።   ለነገሩ ኢትዮጵያውያን ፈረንጅ የሚለውን ብዙም አለመከታተላቸው መልካም ሳይሆን አይቀርም። ሰዳቢን ቢከታተሉት ትርፉ ብስጭት ነው። ስለዚህ የፈረንጆቹን ዲስኩር ትተን የራሳችን ስንመረምር ኢትዮጵያ እጹብ ድንቅ የሥራ ድርሻ እንዳላት እናያለን። እንቅፋትና፡ እሾህ፣ ኮረብታና ቁልቁለት፤ ወጣ ገባ መሰናክልና ችግር  በመንገዷ ቢያጋጥምም፤  ለብዙ ሺህ አመታት ኢትዮጵያ የእግዚአብሔርን ህጎች ጠብቃ የኖረች አገር ናት። ከምእራብ የተወረሰው ዘመናዊ አስተሳሰብ ባህሏን እና ሥርአቷን አጥፍቶት ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያ ገና በሌሊት እንደምትነሳ፣ ስዎቿንም በማለዳ እንደምታሰማራ፣ የወይን ፍሬም እንደምትተክል፣ መቀነቷን ታጥቃ ክንዷንም እንደምታበረታ፣ ጣቶቿም እንዝርት እንደሚይዙ፣ ለችግረኛም እጇን እንደምትዘረጋ፣ ስጋጃም እንደምትሰራ፣ የርኅራኄም ህግ በምላሷ እንዳለ፣ ለባልዋም ዘውድ እንደሆነች፡ ስንዱ ሴት ነበረች። ስሟም ጽዮን ይባል ነበር።

ከአካሏ በነጣቂዎች ተነጥለው የተወሰዱባት ሱዳን፣ የመን፣ ሶማሊያ፣ ጂቡቲ እና ኤርትራም ኢትዮጵያ ናቸው። ኢትዮጵያ የሆኑት እነዚህ አካሎቿ በመጨረሻው ዘመን ከአውሬው ጋር ሆነው በጽዮን ላይ ዘመቱባት። የሚሆነው ተፈጸመ። አሁን ግን ጊዜ አልቋልና ወደጽዮን በተራ በተራ መመለሳቸው አይቀርም።
 
ኢትዮጵያ ለእግዚአብሔር የተመረጠችው ከመጀመሪያው ነው። የኢትዮጵያ ቅኔ የሚጀምረው ከሳሌም ንጉሥ ከመልከጸዴቅ ነው።

ንግሥተ አዜብም ከኢትዮጵያ ተነስታ ጥበብን ፍለጋ ተጓዘች። ጥበብም አገኛት። ከስሎሞንም ይበልጣል።

ንጉሱ ሰሎሞንም በማኃልየ፡ መኃልይ፡ ዘሰሎሞን፡ የእግዚአብሔር ጸጋ ከንግሥተ አዜብ ጋራ እንደመጣ፣ እስራኤል ልጃገረዶች ሁሉ የተመረጠችውም እሷ እንደሆነች ቅኔ ተቀኜላት።  እሷም በኢትዮጵያ ደርሳ አፏን በጥበብ ከፈተች። እንዲህም አለች፡
 
"
አቤቱ የቅዱሳን ቅዱስ፣ የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ ጥበብን እንድከተላት ታድለኝ ዘንድ እፀልያለሁ። እታነጽባት ዘንድ እንጅ እንዳልፈርስባት አድለኝ። አሸንፍባት ዘንድ እንጅ እንዳልሸነፍባት አድለኝ። እሰወርባት ዘንድ እንጅ እንዳልናድባት አድለኝ። እጎለምስባት ዘንድ እንጅ እንዳልደክምባት አድለኝ። እቆምባት ዘንድ እንጅ እንዳልወድቅባት አድለኝ። እመረኮዝባት ዘንድ እንጅ እንዳልፍገመገምባት አድለኝ። እጫወትባት ዘንድ እንጅ እንዳልንሸራተትባት አድለኝ። እንሳፈፍባት ዘንድ እንጅ እንዳልሰጥምባት አድለኝ። እፀናባት ዘንድ እንጅ እንዳልነቀልባት አድለኝ። እሰራባት ዘንድ አድለኝ።…….ለኔ ብቻ አይደለም ለአገሬ ለኢትዮጵያ ሰዎች ጭምር እንጅ።…….. እግዚአብሔር በጽዮን ዘርን በኢየሩሳሌም ማደሪያን ሰጥቶናል። ደግሞም ከመረጣቸው ከያዕቆብ ዘር ጋር ክፍል ሆንን ማደሪያውንም ከኛ ጋር ታድር ዘንድ አድርጓልና።" ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ የገባች እለት ንግሥተ ሳባ ለሌዋውያን የነገረቻቸው።

ንጉሥ ሰሎሞን ካህኑ ሳዶቅን እንዲህ ብሎ ነገረው፦ ንግሥቲቱ በመጣችበት ወቅት በሌሊት እንዲህ አሳየኝ። በኢየሩሳሌም ዋልታ እንደቆምኩ በይሁዳ አገር ከሰማይ ፀሐይ ወረደች። እጅግም አበራች። ቆይታም ጠፋች። ለሃገረ ኢትዮጵያም አበራች። ሁለተኛም ወደ ይሁዳ ምድር አልተመለሰችም። ክብረ ነገስት ፶ወ፮ በእንተ ግብአተ ስዶቅ ካህን ውሂቦ ሞፃ

ፀሐይ ከይሁዳ አገር ተነጥቃ በኢትዮጵያ ለምን አበራች?

መመረጥ ምንድን ነው?

መመረጥ በአፀደ ሥጋ ኑሮን ከጨረሱ በኋላ በአፀደ ነፍስ ወደጽድቅ ቦታ መሄድን አያመለክትም። የተመረጡ ሰዎች የፀደቁ ሰዎች ማለት አይደለም። በማቴዎስ ፳፬፤ ፳፬ ሃሰተኞች ክርስቶሶችና ሃሰተኞች ነቢያት ይነሳሉ፤ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ፤- የሚለው የእግዚአብሔር ቃል ሰዎች የሚመረጡት ገና ክፉና ደጉን ከመሥራታቸው በፊት እንደሆነ ያሳያል። የማቴዎስ ወንጌል በምዕራፍ ፳፪ ከቁጥር ፩ ጀምሮ እንደሚያስተምረን፦ ኢየሱስ ለካህናት አለቆችና ለፈሪሳውያን በምሳሌ ነገራቸው። እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሠርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች። የታደሙትንም (እብራውያን) ወደ ሠርጉ (ወደ ክርስትና) ይጠሩ ዘንድ ባሮቹን ላከ፤ ሊመጡም አልወደዱም። ደግሞ ሌሎችን ባሮች ልኮ፦ የታደሙትን እነሆ ድግሴን አዘጋጀሁ፦ ኮርማዎቸና የሰቡት ከብቶቸ ታርደዋል። ሁሉም ተዘጋጅቷል። ወደ ሰርጉ ኑ በሏቸው፡ አለ። እነሱ ግን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ። የቀሩትም ባሮቹን ይዘው አንገላቷቸው፣ ገደሏቸውም። ንጉሡም ተቆጣ ፣ ጭፍሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፣ ከተማቸውንም አቃጠለ። በዚያን ጊዜ ባሮቹን፦ ሰርጉስ ተዘጋጅቷል፦ ነገር ግን የታደሙት የማይገባቸው ሆኑ፤ እንግዲህ ወደመንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ፡ አለ። እነዛም ባሮች ወደመንገድ ወጥተው ያገኙትን ሁሉ፡ ክፉወችንም፤ በጎዎችንም ሰበሰቡ፤ የሠርጉንም ቤት ተቀማጮች ሞሉት። ንጉሡም የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዛ የሠርግ ልብስ ያልለበሰ (ሥርአትና ህግን ያልጠበቀ) አንድ ሰው አየና፦ ወዳጄ ሆይ፦ የሠርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ? አለው። እርሱም ዝም አለ። በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን፦ እጁን እና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡ አለ። የተጠሩ ብዙወች የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።

ከላይ እንዳየነው የተመረጡት የብሉይ ኪዳን እብራዉያን ሆነው ክርስቶስን ባለመቀበላቸው መመረጥ በነሱ አላከተመም። የክርስቶስ ባሮች (ሐዋርያት) ከመንገድ ሆነው ሁሉንም ጋበዙ። የተጋበዙትም በሙሉ የሠርጉን ቤት ሞሉት። ሁሉም ግን የተመረጡ አይደሉም። የተመረጡት በሠርጉ የተገኙ፣ ሲገኙም ሥርአቱንና ህጉን የጠበቁ ናቸው። እነዚህ ህዝቦች በብሉይ ኪዳን እብራዉያን ምትክ በእግዚአብሔር የተመረጡ የአዲስ ኪዳን ተረካቢዎች ናቸው። ህግና ሥርአትን ትተው እምነት ብቻ ያድናል ያሉ አልተመረጡም። 

ከፍ ብሎ እንዳየነው መመረጥ ያለው ከፉና ደግን ከመሥራት በፊት ስለሆነ ከሠርጉ ተጠርተው የተገኙ፣ ተገኝተውም ሥርአቱን የጠበቁ የእግዚአብሔር ባለአደራወች በእግዚአብሔር የተመረጡት በሠርጉ ከመገኘታቸው በፊት ነው። ክርስትና የመጣው ለሁሉም ነው። ለክርስትና የታደሙት እብራውያን ክርስትናን አልተቀበሉትም። ህዝብና አህዛብም ተጋብዘው ክርስትያኖች ሆኑ። በክርስትና እምነት የተገኙ፣ ተገኝተውም የእግዚአብሔርን ህግና ሥርአት የጠበቁ እነሱ እስራኤል ናቸው። ከእብራውያንም ከአህዛብም በፊት የተመረጡ ናቸው።

ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር የተባለች ምርጥ መሆኗ ከላይ በተዘረዘረው ምክንያት ነው። በተዋህዶ እምነት የቆዩ፣ ሥርአቱንና ህጉን የጠበቁ ኢትዮጵያውያን የተመረጡ ናቸው። መመረጥ ገና ክፉና ደጉን ከመሥራት በፊት ስለሆነ ኢትዮጵያም የተመረጠችው ቀደም ብላ ነው።

እግዚአብሔር ከኛ የሚጠብቀውን እንድናውቅ፣ አውቀንም በእግዚአብሔር መንገድ በቀና እርምጃ እንሄድ ዘንድ፤ እግዚአብሔርንም አባታችን ሆይ ብለን እንጠራው ዘንድ፣ እሱም ልጆቼ ብሎ ይጠራን ዘንድ፤ ኢትዮጵያ ቀደም ብላ በእግዚአብሔር የተመረጠች መሆኗን ከዚህ በታች እናያለን። በእምነት ውስጥ የሌሉ ኢትዮጵያውያንም ቢሆኑ መንፈሳዊውን ነገር በመንፈስ መረዳት ባይችሉ፤ ከዚህ በታች የተጠቀሱትን በአይን የሚታዩና በእጅ የሚጨበጡ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራወች አይተው አገራቸው የእግዚአብሔር መሆኗን አውቀው እምነትታቸውና ተስፋቸው እግዚአብሔር እንዲሆን መጸለይ አለብን።                   

እሥራኤል ዘመንፈስ ዘኅልቁ

በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ምርጥ ህዝብ የሆኑት እብራውያን በአህዛብ የጣኦት አምልኮ እንዳይማረኩና ከእግዚአብሔር መንገድ እንዳይወጡ ከአህዛብ ጋር እንዲጋቡ አልተፈቀላቸውም ነበር። በዚህ ጊዜ የእብራውያን ቁንጮ የሆነው ሙሴ በእግዚአብሔር ፈቃድ ባለቤቱ ኢትዮጵያዊት ሆነች። የሙሴ እህት ማርያም ወንድሟ ሙሴ ኢትዮጵያዊት ለምን አገባ ብላ በመቃወሟ እግዚአብሔር በለምጽ ቀጥቷታል። ሙሴ ኢትዮጵያዊቷን ማግባቱ የተባረከለት የእግዚአብሔር ህግ በየአጋጣሚው የሚቀያየር ሆኖ አይደለም፤ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን አስቀድመው የተመረጡ በመሆናቸው ነው።

እሥራኤል ዘመንፈስ በአሞጽ

የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የኢትዮጵያ ልጆች እንደ እስራኤል ልጆች የተመረጡ መሆናቸውን በነብዩ በአሞጽ አንደበት በቀጥታ ተናገረ። እንዲህም አለ፦ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን?

እሥራኤል ዘመንፈስ በመዝሙረ ዳዊት

እግዚአብሔር በሚወደው አገልጋዩ በዳዊት አንደበተ ትንቢት እንዲህ አለ፦ መኳንንት (ጳጳሳት) ከግብጽ ይመጣሉ፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች። ዳዊት በትንቢት እንዲህ ተናግሮ ኢትዮጵያ የታቦተ ጽዮን መኖሪያ ሆነች፣ ክርስትናም በአዋጅ የመንግሥት ኃይማኖት ሆኖ የተደነገገባት በዓለም የመጀመሪያዋ አገር ሆነች፤ ጳጳሶቿም የማርቆስ ወንጌልን ከጻፈው ከቅዱስ ማርቆስ መንበር ከግብጽ መጡ። የዳዊት ትንቢት በሚያስደንቅ ሁኔታ በኢትዮጵያ ተገለጠ።

እግዚአብሔር በመረጣት ምድር ድንቅ ነገሮችን አደረገ

እግዚአብሔር በኢትዮጵያ የሠራውን ሥራ በማየት የተመረጠችው መልካሚቷ ምድር መሆኗን አስተውሉ።

ጽዮንን በኢትዮጵያ አደረገ

በምድር ላይ እግዚአብሔር ያልባረከው የትኛውም ቦታ ሊሸከማት የማይችል የእግዚአብሔር ታቦት ጽዮን በኢትዮጵያ እንድትኖር አደረገ። እብራውያን ክርስቶስን እንደማይቀበሉ እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለሚያውቅ ጽዮን በእብራውያን እጅ እንድትቆይ  አልፈቀደም። ለዚህም ነው በተመረጡት፣ አዲስ ኪዳንን በሚቀበሉት በኢትዮጵያውያን መካከል እንድትኖር ፈቃዱ የሆነው። እነሆ የሚመረጡት አስቀድመው ተመረጡ።

ቅዱሳንንም ወደ ኢትዮጵያ መራ

አንዱ አገር ሌላው አገር ምን እንደሆነ ለማወቅ በማይችልበት ጥንተ ዘመን በክርስቶስ አገልጋይነታቸው ምክንያት ከተለያዩ አገሮች በአሳዳጆች የተሰደዱ፡ ምርጥ፣ ምርጥ ቅዱሳን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ከተለያዩ ቦታወች ሳይተዋወቁና ሳይመካከሩ በተለያየ ጊዜ ተነስተው የሁሉም መድረሻቸው አንድ ኢትዮጵያ ሆነች። በእርሷም ሆነው ለዘላለም እግዚአብሐርን ቀደሱ። 

መዳህኒታችንና እናቱ በስደት ጎበኟት

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከብጽእት ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር በተሰደደበት ዘመን እሱም እናቱም በግብጽ በኩል ወደኢትዮጵያ መጡ፣ አረፉባትም።
የመዳህኒታችንና የእናቱ የድንግል ማርያም ስደት።
ዮሴፍና ሶሎሜም አብረው አሉ

የመላእክት ዜማ ለኢትዮጵያ ተሰጠ

ቅዱስ ያሬድ በመንፈስቅዱስ መሪነት በምድር ላይ ተፈልስፎ የማያውቅ የምስጋና መዝሙረ ኖታወችን አፍልቋል። ኖታወቹ የፈለቁት ለምስጋና እንጅ ለዘፈንአይደለም። በዓለም ላይ የሙዚቃ
ኖታን የፈጠሩ አገሮች እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው። እነዚህም ሃገሮች የሙዚቃ ኖታን የፈጠሩት ለዘፈን እንጅ እግዚአብሔርን ለማመስገኛ አይደለም። በምድር ላይ እግዚአብሔርን ለማመስገን የተፈጠረ ኖታ የኢትዮጵያ ብቻ ነው።

መለኮት ማህደሩን ከአንድ አለት በኢትዮጵያ ሠራ

ቅዱስ ላሊበላ በምድር ላይ ተሠርቶ የማያውቅ ከአንድ ድንጋይ የተጠረበ፤ ያልተሰፋ፤ ያልተገጣጠመ፡ ያልተገነባ፤ ያልተለሰነ፡ አንድ ወጥ የሆነች ዳግማዊት የኢየሩሳሌም ከተማን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በኢትዮጵያ ሠራ። ድንጋይ ጠርበው የዋሻ ውስጥ ቤተክርስትያን የሠሩ ሌሎች አገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ከአንድ አለት የተጠረበች ከተማን የሠራ አገር ከኢትዮጵያ ውጪ ሌላ የለም። ይህችም ከተማ የእግዚአብሔር ማደሪያ ኢየሩሳሌም ናት፣ ከኢትዮጵያ በቀር በሌላ ቦታም የለችም።

ኢትዮጵያ ደጋግማ ጥበብን ከልቧ አነቃች

ማከዳ

ኢትዮጵያዊቷ ማከዳ ንግሥተ አዜብ ጥበብን ፈልጋ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፣ ያለ አማካሪና ያለ አስተማሪ እግዚአብሔርን አመሰገነች። ንጉሥ ሰሎሞንን በትህትና እንዲህም አለችው፦ "እኔ እግርህን እንዳጥብ፣ ጥበብህን እንድሰማና እውቀትህንም ልብ እንድል፣ ለመንግሥትህ እንድገዛና በጥበብህም እደሰት ዘንድ ከሴቶች ባሪያወች ሁሉ ከምታንሰው እንደ አንዷ በሆንኩ በወደድኩ። መልስህ፣ የቃልህ ጣእም፣ ያማረው አካሄድህ፣ የተዋበው ንግግርህና የቃልህ ጣእም ቅልጥፍና ምን ያህል ደስ አሰኘኝ። ልብን ያስደስታል፣ አጥንትን ያለመልማል፣ ልብን ይመግባል። ያጠራልም ከንፈሮችን ያስውባል፣ መርገጫየን ያጠነክራል። ጥበብህ ያለመለኪያ፣ ሃሳብህ ያለጉድለት ነው። በጨለማ ውስጥ እንዳለ መብራት፣ በገነት እንዳለ ሮማን፣ በባህር ውስጥ እንዳለ እንቁ፣ በከዋከብት መካከል እንዳለ የንጋት ኮኰብ፣ በጉም ውስጥ እንዳለ የጨረቃ ብርሃን፣ እንደ ጥባት ብርሃንና በሰማይ ውስጥ እንዳለ የፀሐይ አወጣጥ እንድሆንክ አይሃለሁ። እኔን እዚህ ያደረሰኝና አንተን ያሳየኝ፣ የባህርንም ደጃፍ ያስረገጠኝንና ቃልህን ያሰማኝን አምላክ አመሰግነዋለሁ" አለችው። ንጉሥ ሰሎሞንም እንደዚህ መለሰላት፦ "ጥበብና ማስተዋል ካንቺ ነቃች። እኔስ የእስራኤል አምላክ  ከሱ በፈለግሁትና በለመንኩት መጠን ሰጠኝ። አንቺ ግን የእስራኤልን አምላክ ሳታውቂ የድንኳኑን ጠባቂ ቋሚ የእስራኤል አምላክ ማደሪያ በሆነች ሰማያዊት ቅድስት ጽዮን ፊት የምቆም የምላክና የምመላለስ የአምላኬ አነስተኛ ባሪያ የሆንኩ እኔን ታይ ዘንድ ይህንን ጥበብ ከልብሽ አነቃሽ።" አላት። ሳታውቀው እግዚአብሔር ጥበብን ፈለገችው፣ ጥበብ እግዚአብሔርም አገኛት፣ በብዙም ሰጣት።  ማከዳ የእሥራኤልን አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ  ጥበብ እግዚአብሔርን በልቧ ይዛ ተመለሰች።  ከአብርሃም በቀር እግዚአብሔርን ማከዳ ባገኘችበት መንገድ ያገኘው የለም።

ንግሥተ አዜብ በሰሎሞን ቤተመንግሥት

ጌታችን መዳህኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ንግስተ አዜብ (ማከዳ) እንዲህ አለ። ንግሥተ አዜብ በፍርድ ከዚህ ትውልድ ሰዎች ጋር ተነስታ ትፈርድባቸዋለች። የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፤ እነሆም ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ።

ንግስቷ ማከዳ ያለአስተማሪ እግዚአብሔርን የመሻትን ነገር ከልቧ ያነቃችው በእግዚአብሔር ጥበብ ከኢትዮጵያዊነቷ ነው።

አቤሜሌክ

ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ነቢዩ ኤርምያስን በጉድጓዱ ውስጥ እንዳኖሩት ሰማ። የይሁዳ ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ነበር። አቤሜሌክም ከንጉሡ ቤት ወጥቶ ንጉሡን እንዲህ አለው፦ "ጌታየ ንጉሥ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ነቢዩን ኤርምያስን በጉድጓድ ውስጥ በመጣላቸው፣ በእርሱ ላይ በማድረጋቸው ሁሉ ክፉ አድርጋዋል፣ በከተማይቱም ውስጥ እንጀራ ስለሌለ በዛ በረሃብ ይሞታል።" ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክን፦ "ከአንተ ጋር ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ውሰድ፣ ነቢዩም ኤርምያስ ሳይሞት ከጉድጓድ አውጣው ብሎ አዘዘው።" አቤሜሌክም ሰዎቹን ይዞ በአሮጌ ጨርቅ ጎትቶ ኤርምያስን ከጉድጓድ አውጣው። ኢትዮጵያዊው ኤርምያስን ከጉድጓዱ ለማውጣት የተነሳሳው ማንም ሳያማክረው፣ ሳይገፋፋው፣ በእግዚአብሔር መሪነት ማስተዋልን ከልቡ አንቅቶ ነው።

እግዚአብሔርም እንደዚህ ባረከው፦ በምትፈራቸው ሰዎች እጅ አልሰጥህም፣ ፈጽሜ አድንሃለሁ፡ ነፍስህም እንደምርኮ ትሆናለች እንጅ በሰይፍ አትወድቅም፦ በኔ ታምነሃልና።

ንጉሥ ባዜን

ሕጻኑ ልዑል መዳህኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ በእግዚአብሔር መሪነት እጅ መንሻ ለህፃኑ ልዑል ለጌታ ለመስገድ በምስራቅ ኮከብ መሪነት ተመርተው ከሄዱት ሰብአ ሰገል አንደኛው ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ባዜን ነበር። ሰብአ ሰገል ህፃኑን ከእናቱ ከብጽኢት ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር አዩት፦ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሳጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና እጣን ከርቤም አቀረቡለት።
ንጉሥ ባዜን ያለአስተማሪ ጥበብን ከልቡ አነቃ። አጼ ባዜን ጥበብ እግዚአብሔርን ሽቶ ለእግዚአብሔር በረከትን የማቅረብ ምግባርን ከልቡ ያነቃው በእግዚአብሔር ፈቃድ ከኢትዮጵያዊነቱ ነው። 

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ እግዚአብሔርን ለማመሰገን ወደ እየሩሳሌም ሄዶ ወደ አገሩ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ፊሊጶስ ይገናኘዋል። ጃንደረባው በሰረገላው ተቀምጦ የሚያነብበው የኢሳያስ ትንቢት ትርጉም ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ቅዱስ ፊሊጶስ ይነግረዋል። ቅዱስ ፊሊጶስ ስለጥምቀት ሳይነግረው ጃንደረባው "እነሆ ውኃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድን ነው?" ብሎ ይጠመቅ ዘንድ ያለመሪ እራሱ ጠየቀ። ይህን እግዚአብሔርን የመሻት ጥበብ ከልቡ አንቅቶ፣ እራሱ ጠይቆ ተጠመቀ። ሳያውቅ ጥበብ እግዚአብሔርን መሻትን ከልቡ ያነቃው ጃንደረባው በእግዚአብሔር ቸርነት ከኢትዮጵያዊነቱ ነው።

አብርሃና አጽብሃ

ልጅ እግሩ ንጉሥ አብርሃ ሰው ሳያማክረው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የጌታን ወንጌል ከጻፈው ከቅዱስ ማርቆስ መንበር ጌታችን መዳህኒታችን ባዘዘው መሠረት ቤተክርስትያን የሐዋርያትን ቡራኬ እንድታገኝ ወደ ቅዱስ ማርቆስ መንበር መልእክተኛ ላከ። ቤተክርስትያንም በኢትዮጵያ ጸናች።፡ አብርሃና አጽብሃ እንዲሁም እናታቸው እንስበካችሁ፣ ወይም እናስተምራችሁ ብሎ ወደነሱ የመጣ የሰው አስተማሪ ወይም አበረታች ሳይኖር፣ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ጥበብ አግዚአብሔር መሻትን ከልባቸው አነቁ። የቅዱስ ዳዊት ትንቢት ኢዛናን ምክንያት አደረገ። አብርሃና አጽብሃ ያለአስተማሪ እግዚአብሔርን የመሻት ተፈጥሯቸው የተገኘው በእግዚአብሔር ፈቃድ ከኢትዮጵያዊነት ነው።  

እስካሁን እንዳየነው ከማንም አገርና ህዝብ በተለየ ሁኔታ ኢትዮጵያውያን እግዚአብሔርን የፈለጉት ያለአነሳሽ ወይም ያለ አስተማሪ ጥበብን ከልባቸው እያነቁ ነው። በቅዱሳን መጻሕፍት ኢትዮጵያውያን በተጠቀሱበት አንቀጾችና ምእራፎች ሁሉ የኢትዮጵያውያን መልክ ሳይለወጥ እንደዚህ ሆኖ ነው የተነገረው። አጋጣሚ ነው እንዳይባል ሁልጊዜ ነው። በጽሁፎቹ ላይ የሰው እጅ አለበት እንዳይባል መልእክቱ በሰም ሳይሆን በወርቅ መልክ ነው የቀረበው። መልእክቶቹ የተጻፉትም በተራራቀ ዘመን ነው። 
 
ኢትዮጵያ እስራኤል ዘመንፈስ የምትባለው ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ነው። እውነተኛዋን ኃይማኖት እንድናውቅ እግዚአብሔር በትንቢተ ኢሳያስ ምእራፍ ፲፱ ቁ ፳፬ ህዝቤ ግብጽ፣ የእጄ ሥራ አሦር፣ እርስቴም እስራኤል የተባረክ ይሁን። በዚያ ቀን እስራኤል ለግብጽና ለአሦር ሶስተኛ ይሆናል። ብሎ ተናገረ። እግዚአብሔር በነቢዩ በኩል የሚነግረን ግብጽ፣ ሶሪያና እስራኤል አንድ ላይ ሆነው መስዋእት የሚያቀርቡበት እምነት የተባረከ እንደሆነ የጊዜው ምልክትም ወራሪወች ግብጽን በሚይዙበት ዘመንና የጥፋት ከተማ የተባለች ከተማ በምትጠራበት ጊዜ ነው። የጥፋት ከተማዋም ካይሮ ትባላለች።   በዚህ ዘመንም ሶስቱ አንድ ላይ መስዋእት እንደሚያቀርቡ አስተውሉ ብሎ ነው። ካይሮ በተሰየመችበት ዘመን ከግብጽና ሶሪያ ቤተክርስቲያኖች ጋር በአንድነት በቤተመቅደስ መስዋእት ያቀረበች አገር ኢትዮጵያ ናት። አብርሃና አጽብሐ ወደ ቅዱስ ማርቆስ መንበር መልእክተኛ የላኩት ይህ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ግድ ስለሆነ  ነው።      

እስራኤል ዘመንፈስ ማለት ክርስቲያን ማለት ከሆነ፤ ግብጽና ሶርያ እንደ ኢትዮጵያ ለምን እስራኤል አልተባሉም?

የእግዚአብሔርን ህግና ሥርአት የምትጠብቅ ቤተክርስትያን እሷ ኢየሩሳሌም ናት። የክርስቶስ ተከታይ የሆነ የእግዚብሔርን ህግና ሥርዓት የሚጠብቅ ህዝብ እስራኤል ነው። የእግዚብሔርን ህግና ሥርዓት ጠብቃም የመንግስት አስተዳደሯም በእግዚአብሔር ህግ የሚመራ ከሆነ ይህቺ አገር እስራኤል ናት። በአዋጅ ክርስትናን የመንግስት ሃይማኖት ያደረገች፣ መሪየም ክርስቶስ ነው ያለች ሃገር የመጀመሪያዋ፣ ደግሞም ካንድ ሺህ ስደስት መቶ አመታት በላይ በዚህ ሥርአት ጸንታ የቆየች አገር ኢትዮጵያ በምድር ላይ ብቻ ናት። ከአብርሃና አጽብሐ ጀምሮ ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ "ኃይማኖት የግል ነው፣ ሃገር የጋራ ነው" እስካሉበት ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ ህግን ተብቃ ኖረች። ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯልና በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ ፳፩ ቁጥር ፵፫ እንደተጻፈው ለእሥራኤል ዘስጋ እንዲህ አላቸው የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች። በዚህም ቃሉ የእግዚአብሔር መንግሥት በኢትዮጵያ በአዲስ ኪዳን ጸንታ ቆየች። ብዙ የግብጽና የሶሪያ ሰዎች ምንም እንኳን በእውነተኛዋ የሃይማኖት መስመር ቢሄዱም በሃገሮቻቸው ክርስትና የመንግስት ኃይማኖት ስላልነበረ ሃገሮቻቸው እስራኤል አልተባሉም።

ከብዙ መቶ አመታት በፊት አባ ህርያቆስ በቅዳሴ ማርያም፦ በአራቱ ማእዘን ኃይማኖት ሲጠፋ እስከ እለተ ምጽአት ወልድ ዋህድ ስትል ርዕሷ አክሱም ሀገር መላ ኢትዮጵያ ትኖራለች። ብለው ጻፉ። እንዳሉትም ባሁኑ ሰዓት የእግዚአብሔርን መስመር ይከተሉ የነበሩ ብዙወች አዳዲስ ትምህርቶችን ሲያሰለጠኑ ይታያሉ። በተለይም ድንግል ማርያምን በተመለከተ ከሃይማኖት መስመር የወጡ  ብዙ ፍልስፍናወችን ሲራምዱ ይታያሉ።

እብራውያን እስራኤል ዘሥጋ የተባሉት የሰው ልጅ በክርስቶስ እንዲድን ትንቢት የሚፈጸመው በነሱ ስለሆነ ነበር። እስራኤል ዘመንፈስ ደግሞ የክርስቶስ የፍርድ ቀን ትንቢት የሚፈጸመው ክርስቶስ እራሱ እንደተናገረው ንግሥተ አዜብ ፈራጅ ሆና ነው። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ይህ የእግዚአብሔር ቃል ግን አያልፍም።   

ከኢየሩሳሌም ስለመሰደድ

የኢትዮጵያ ድሃ መሆን እጅግ ብዙ የኢትዮጵያ ሰዎችን የመራብ፣ የመጠማትና የመታረዝ ችግር አድርሶባቸዋል። የሚበላው ያጣ ሰው ምግብ ለማግኜት እንዲረዳው በሌላ ጊዜ የማይሰራውን ሥራ ሊሰራ ይችላል። ችግር አንዳንዶችን ወደ ስርቆት፣ አንዳንዶችን ወደ ሴት አዳሪነት፣ አንዳንዶችን ደግሞ ስብእናን በሌላ በተለያየ መልክ ወደመሸጥ ይገፋፋል። የኢትዮጵያ ድሃ መሆን ፈተና ነው። በችግር ምክንያት ወይም ብዙ የሚጎሳቆሉ ሰዎችን በማየት አንድ የኢትዮጵያ ሰው ኢትዮጵያዊነት ብዙም ስሜት የማይሰጠው ሊሆን ይችላል። አንዳንዶቹ ደግሞ ምንም እንኳን በድህነት ቢጎሳቆሉም ኢትዮጵያዊነታቸውን አጥብቀው የሚወዱ አሉ። አንዳንድ ሰዎች የራሳቸው የሆነው ነገር በሌሎች እንዳዩት አይነት የቁሳቁስ ጥቅም የማያስገኝ ቢሆን የራሳቸውን አጥብቀው ለመያዝ ቸለልተኛ ይሆናሉ። ለቁሳቁስ ሲባል የራሳቸውን ጣሉ የሚያስብል የአእምሮ ወቀሳ እንዳያገኛቸው የራሳቸውን ለመጣል ከጥቅም ጋር በቀጥታ የማይገናኝ ሌላ ትንሽ ሰበብን ይሻሉ። በዚህ ላይ የራሳቸውን የሚያስጥለው ነገር በቀጥታ የቁሳቁስ ጥቅም እንኳን ባይኖረውም ለሌሎች ጥቅም ሰጥቶ ማየታቸው የራሳቸውን ለመጣል ትልቅ ማበረታቻ ይሆንላቸዋል። ብዙ የኢትዮጵያ ሰዎች በዚህ መንገድ በእምነት ከኢየሩሳሌም ተሰድደው ወደባቢሎን አምርተዋል። የምዕራቡ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ሰዎችን አእምሮ እንዴት ወረረ? ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ሰዎች የራሳቸውን ለምን ናቁ? የምዕራቡንስ እንዴት አደነቁ? የኢየሩሳሌም በረከት  እና የባቢሎን ጌጣጌጥ እንዴት ይለያሉ?አሁን በምድር ላይ የሚኖርን የሰው ልጅ የሆነውን ሁሉ የሚያባብለውን የምዕራቡን ብልጽግና እስኪ እንጎብኜው። የምዕራባውያን ብልጽግና ከምን ፈለቀ? ምንድንስ ነው?ኑ ወደ ጽዮን ተራራ ።

ወደ ገጽ ፪ ለመሄድ ከዚህ ይጫኑ
 two
 HOME