የተወደዱ ሆይ ጥር ሃያ ሁለት ቀን አምስት መቶ አስራ ስድስት ዓመት ምህረት በንጉሡ በእዮስጦስ ከተላኩት ከኤፍራስዮስ ልጅ ከካህኑ ከአብርሃም ጋር ሆነን  ከንኡማን ተነስተን ከአረቦች ንጉሥ ከሙንድሂር ጋር ሰላም ለመፍጠር ወደሂርታ አመራን።  ሰለእርሳቸውም በመጀመሪያው ደብዳቤያችን ገልጸናል። ጉዳያችን በተመለከተ ላደረጉልን እርዳታ ከምእመናን ጋር አመስግነናቸዋል።  ከዚህ ቀደም ስለጻፍነውም ሆነ አሁን ስለጻፍነው ጉዳይ ያውቃሉ።

ለአሥር ቀናት በደቡባዊ ምስራቅ አቅጣጫ በበረሃ ተጉዘን ከአሸዋ ተራራ ባሻገር ከሚገኘው በአርብኛ ቋንቋ ራማላህ ከሚባለው ቦታ ደረስን። ከሙንድሂር ሠፈር ስንደርስ መአዲያዎችን አገኘን። እነሱም፥ "ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? የናንተን ክርስቶስ ሮማውያን፣ የፔርዢያ ሰዎችና የህመራይ ሰዎች አልተቀበሉትም" አሉን። እንዲህ ብለው ስለተሳለቁብን በጣም ሃዘን ተሰማን። ጭንቀትም አደረብን ምክንያቱም እዛው እኛ ባለንበት የህመራይ ንጉሥ መልእክተኛ ትእቢት የተሞላበት ደብዳቤ ይዞ ለአረቡ ንጉሥ ለሙንድሂር ሰጠው። ደብዳቤውም ከዚህ በታች ያለው ነው።

"ወንድሜ ንጉሥ ሙንዲህር ሆይ - በአውራጃችን ኩሾች (አክሱሞች) የሾሙት ንጉሥ እንደሞተ ክረምት መጣ። ክረምትም በመሆኑ ኩሾች (አክሱሞች) ባህሩን ተሻግረው ወደኛ አውራጃ በመምጣት ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት የክርስቲያን ንጉሥ ሊሾሙ አልቻሉም ነበርና እኔ መላውን የህመራይ ምድር መምራት ጀመርኩ። በዚህ ጊዜ በህመራይ በክርስቶስ የሚመኩ ክርስቲያኖችን ሰብስቤ አጎርኩና እንደኛ አይሁድ እንዲሆኑ አዘዝኳቸው። እነ ዘካሪያስና እነ ሚካኤልን ጨምሮ ሁለት መቶ ሰማንያ የክርስቲያን ካህኖችን ቤተክርስቲያናቸውን ከሚጠብቁት ኩሾች (አክሱሞች) ጋራ ገደልኳቸው። ቤተክርቲያናቸውንም የኛ የአይሁዶች መቅደስ አደረኩት። ከዛም አንድ መቶ ሃያ ሺህ ሠራዊት ይዤ ወደ አክሱሞች ዋና ከተማ ወደ ናጅራን ገሰገስኩ። ለጥቂት ቀናት ከተማዋን ከአጠቃሁ በኋላ ልቆጣጠራት ስላልቻልኩ መሃላ ማልኩላቸው። መሃላ ብምልላቸውም ለጠላቶቼ ለክርስቲያኖች ቃሌን ለመጠበቅ አልወደድኩም። አሠርኳቸውና ያላቸውን የወርቅና የብር ንብረት እንዲያመጡ አስገደድኳቸው። አመጡም። እኔም ሰበሰብኩ። ጳውሎስ የተባለውን ዋናውን ካህናቸውን ፈለግሁት። ሞቷል ብለው ሲነግሩኝ መቃብሩን እስኪያሳዩኝ ድረስ አላመንኳቸውም ነበር።  የሱንም አጽም ከመቃብር አውጥቼ አቃጠልኩት። ካህኖቹን እና በቤተክርስቲያን ውስጥ የተደበቁትን ክርስቶስን እና መስቀሉን እንዲክዱ አስገደድኳቸው። እነሱ ግን እምቢ አንክድም፥ እሱ የቅድስት ድንግል ማርያም ልጅ እግዚአብሔር ነው እያሉ ለሱ ሲሉ መሞትን መረጡ።  

"አለቃቸው በእኔ ላይ ብዙ ነገር ተናገረ፣ ሰደበኝም። ስለዚህ አዋቂዎቻቸው በሙሉ እንዲገደሉ አዘዝኹ። ሚስቶቻቸውንም አመጣንና ባሎቻቸው ስለክርስቶስ እያሉ ሲታረዱ እያዩ ክርስቶስን እንዲክዱ ጠየቅናቸው። ሚስቶቻቸውም ክርስቶስን ለመካድ አልፈለጉም። የጽዮን ልጃገረዶች የተባሉት መጀመሪያ እኛ እንታረድ አሉ። የአዋቂዎቹ ሚስቶች ግን የጽዮንን ልጃገረዶች ተቆጧቸው ፥ መሞት ያለብን ከባሎቻችን በኋላ ነው አሏቸው። ንጉሥ ሊሆን ከነበረው ሚስት ከርኹሚ በቀር ሁሉም እንዲገደሉ አደረግን።  እሷም ክርስቶስን ክዳ አይሁድ ሆና ያላትን ንብረት እንደያዘች ለልጆቿም ምህረት አግኝታ እንድትኖር ጠየቅናት። ሄዳ እንድታስብበትም በኛ ወታደሮች ታጅባ ወደ ቤቷ ላክናት።

"ይሁንና ከእውቀት ጊዜዋ ጀምሮ በአደባባይ ታይታ የማትታወቀው ይህች ሴት ክንብንቧን አውልቃ በየመንገዱ እየዞረች እንዲህ እያለች መጮህ ጀመረች፥ 'የናግራን ሴቶች፣ የኔ ክርስቲያኖች፣ አይሆዶችም የሆናችሁ፣ ጣኦትም አምላኪዎች ሁሉ፥ የማን ዘር እንደሆንኩ፣ የማን ክርስቲያን ልጅ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ። ወርቅና ብር፣ የወንድና የሴት አገልጋዮች፣ ሰፊ መንደርና የሃብት ምንጭ እንዳለኝ ታውቃላችሁ። አሁን ባለቤቴ ለክርስቶስ ሲል ተሰውቷልና ባል ላገባ ብፈልግ ባለቤቴ ካስተረፈልኝ ሃብት ሌላ አርባ ሺህ ብር፣ የወርቅና የብር ጌጣጌጥ፣ አልማዝና የሚያምሩ ልብሶች አሉኝ። ይህም ሃሰት እንዳልሆነ ታውቃላችሁ። ለሴት ልጅ በትዳር ከምትኖርበት ዘመን የላቀ ደስታ እንደሌላት ታውቃላችሁ።  ደግሞም እራሳችሁን ታውቃላችሁ፥ ከትዳር ጊዜ ጀምሮ ሴት ልጅ በወሊድ ጊዜ ምጥ አለባት። ልጆች ሲሞቱባትና ስትቀብራቸው ሃዘን አለባት። እኔ ግን ከአሁን በኋላ ከሁሉም ነጻ ነኝ። በመጀመሪያው የትዳሬ ቀን ደስ ተሰኘሁ። አሁን በልቤ ደስታ አምስት ልጃገረድ ልጆቼን ለክርስቶስ አዘጋጅቻለሁ። ተመልከቱኝ ጓደኞቸ፥ መጀመሪያ ጫጉላ ቤትና አሁን ደግሞ በሁለተኛው እንደ መጀመሪያው ክንብንቤን አውልቄ ወደ ክርስቶስ ወደ ጌታየ ወደ እግዚአብሔር፣ ወደ ልጆቼም ጌታ እና እግዚአብሔር፣ በፍቅሩ ዝቅ ብሎ ስለኛ መከራን ወደተቀበለው፡ ወደእሱ እየሄድኩ አያችሁኝ። ከናንተ በቁንጅና የማንስ አይደለሁምና እኔን ምሰሉ።  ቁንጅናየን እንደያዝኩ፣ የአይሁዶች ርኩሰት ሳያገኘኝ ወደ ክርስቶስ እየሄድኩ መሆኔን ተመልከቱ። ቁንጅናየም በጌታየ ፊት ምስክር ይሁን የአይሁድ ክህደት አልደፈረውምና። ወርቅና ብሬን አልወደድኩም፤ የወደድኩት እግዚአብሔርን ነው። ይሄ አመጸኛ እንድክድ ይጠይቀኛል። እግዚአብሔር ያሳያችሁ እኔና ልጆቼ የምናምነውን ክርስቶስ እንዴት እክዳለሁ። የተጠመኩት በስላሴ ስም ነው፣ መስቀሉን እወዳለሁ። ስለሱ እኔና ልጆቼ በደስታ እንሞታለን እሱ ስለ እኛ በሥጋ ተሰቃይቷልና። የሚያሳሳውና ለአይን እና ለሰውነት የሚያጓጓው ሁሉ ሃላፊና ጠፊ ነው። የማያልፈውን ግን ከጌታየ አገኛለሁ። ወገኖቼ ከሰማችሁኝ ትባረካላችሁ። ቃሌን ስሙ፣ እውነትን እወቁ፥ እኔና ልጆቼ የምንሞትለትን ክርስቶስን አፍቅሩ። ከአሁን በኋላ የእግዚአብሔር የሆኑ  ሰላምና ደህንነትን ያገኛሉ። ይህችን ከተማ ለክርስቶስ ሆና ከቀረች ለክርስቶስ ሲሉ የተሰውት ወንድሞቼና እህቶቼ ደም  ገድግዳ ሆኖ ይጠብቃት። እነሆ ክንብንቤን አውልቄ ለጊዜው የቆየሁባትን ከተማ እተዋታለሁ፣ ከልጆቼ ጋር ሆኜ ወደዘላለማዊዋ ከተማ እሄዳለሁ። በዚያ ይሞሸራሉ። ክርስቶስ እንዲቀበለኝ ለምኑልኝ። ባለቤቴ ሦስት ቀን ቀደመኝ።'

"በከተማው የዋይታ ድምጽ ስንሰማ እንዲያጅቧት የላክናቸው ተመልሰው ወደኛ መጡ። ስንጠይቃቸውም ከላይ የተጻፈውን ነገሩን። ርኹሚ በከተማው እየዞረች እያበረታታች እንደሆነ ነገሩን።  በከተማውም ዋይታ ሆነ። አጃቢዎችንም እንዲህ ስታደርግ ዝም ብለው በማየታቸው ልንገድላቸው እስኪቃጣን ድረስ ገሰጽናቸው። ርኹሚም እንደ እብድ ሴት ክንብንቧን አውልቃ ከልጆቿ ጋር መጥታ ያለ ሃፍረት በፊቴ ቆመች። ልጆቿን ለሠርግ እንደታጩ አልብሳ እጅ ለጅ ተያይዘው ከፊቴ ቆሙ። ሹርባዋን (ቁንዳላዋን) ከፊቴ ላይ ፈትታ፣ ጸጉሯን በጆቿ ይዛ ከአንገቷ አጎነበሰችና በጩኸት፥ 'እኔም ልጆቼም ክርስቲያኖች ነን፣ ለክርስቶስ እንሞታለን፣ ወደ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ ወደ ልጆቼም አባት እንሄዳለን፥ ይሄውና አንገታችን ቁረጡ' አለች።

"እኔም ይህን እብደት ካየሁ በኋላ ሰው ነው እንጂ እግዚአብሔር አይደለም ብላ ክርስቶስን እንድትክድ ገፋፋኋት። እሷ ግን ክርስቶስን መካድ አልፈለገችም። ክርስቶስን እንድትክድ በመጠየቄ ምክንያት አንደኛዋ ልጇ ሰደበችኝ። ርኹሚ ክርስቶስን በፍጹም እንደማትክድ ስረዳ ሌሎች ክርስቲያኖችን ለማስፈራራት ከወለሉ ላይ እንዲወረውሯት አዘዝኹ። ከወለሉ ላይ እንደተዘረጋች ልጆቿ ሲታረዱ የደማቸው ፍሳሺ ወደ አፏ ተንቆረቆረ። ከዚህ በኋላ አንገቷ ተቆረጠ።

"በአዶናይ እምላለሁ ርኹሚና ልጆቿ ውብ ቁንጅናቸውን ይዘው መሞታቸው አሳዝኖኛል። እኔና ካህኖቼ ልጆቹ ስለወላጆቻቸው መሞታቸው በህጋችን ተገቢ አልነበረም አልን። በዚህም ምክንያት ወንዶችና ሴቶች ልጆች ከወታደሮች ጋር እንዲያድጉ መደብን። ካደጉ በኋላ አይሁድነትን ከመረጡ መልካም። ክርስቶስን ካሉ ግን መሞት አለባቸው። ለክቡርነትዎ ይህን የምጽፈው ክርስቲያን የተባለ በመካከላችሁ እንዳታኖሩ ለመምከር ነው። በእርስዎ አስተዳደር ውስጥ ያሉ አይሁዶችን ግን በርኅራሄ ይጠብቋቸው። ወንድሜ ሆይ ቃልዎን ይላኩልኝ፣ እኔም የሚፈልጉትን እልክልዎታለሁ።"

ቅዱስ ስምኦን፣ የቤተ አርሻም ጳጳስ ለአባ ስምኦን፣ የጋቡላ ካህን በጥር ወር ፭፻፲፮ (አምስት መቶ አስራ ስድስት) ዓመተ ምህረት የህመራይን ሰማእታት አስመልክቶ የጻፉት ደብዳቤ።

ከአንድ ሺህ አራት መቶ አመታት ከአረቦች ወረራ በፊት አሁን የመን ተብላ የምትጠራው አገር ህመራይ ትባል ነበር። ነዋሪዎቿም ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ማእከሏ አክሱም የሆነች የኢትዮጵያ አውራጃ ነበረች። በአብራሃና አጽብሃ አዋጅ መሠረት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ክርስትና በመሆኑ የህመራይ ሃይማኖት ክርስትና ነበር። በቀሩት የኢትዮጵያ አውራጃዎች እንደነበረው ሁሉ በህመራይም ክርስቲያን አንሆንም ብለው የቀሩ አይሁዶች ነበሩ። እንደሌሎች የኢትዮጵያ አውራጃወችም ህመራይ ንጉሥ ነበራት። የህመራይ ንጉሥም የሚሾመው በማእከላዊው አገር አክሱም በሚገኘው ንጉሠ ነገሥት ነበረ። አንድ ቀን የህመራይ ንጉሥ ከዚህ ዓለም ሲለይ የክረምት ወራት ስለነበረ ሌላ ንጉሥ ለመሾም የአክሱሙ ንጉሠ ነገሥት ወደ ህመራይ ለመጓዝ ክረምቱ አግዷቸው ዘገዩ። በዚህ ጊዜ ከአምስት መቶ አመት በኋላ እንደተነሳችው እንደ ዮዲት ጉዲት አይነት አመጸኛ በህመራይ ተነሳ። ይህም ሰው ሃያ ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የህመራይ ቅዱሳንን አረደ። ከዚህ በታች ያለው ደብዳቤ በቅዱስ ስምኦን በአራማይክ ቋንቋ የተጻፈ ሲሆን ይዘቱ በዚያን ጊዜ በአመጸኛው ይሁዲ ስለተጻፈ ደብዳቤ ነው። ይህ ደብዳቤ አሁን በእንግሊዝ ቤተ መዘክር ውስጥ ይገኛል። Land Ancedota III, 235:12 -243:5 = Ps. Zacharias II 63:23 - 74:13 [192-203], Michael IV 273-276 [II 184-189], cod Mus. Brit. add 14.641 (fol. 157-160)

 HOME