በኑሮ መሻሻል ምን ማለት ነው ?

አንድ ማህበረሰብ ተሻሻለ ወይም በኑሮ አደገ ሊባል የሚችለው የዚህ ማህበረሰብ አባል የሆነ አንድ ቤተሰብ አምና ወይም ታች -አምና የአንድ አመት የቤተሰብ ቀለብ ለማግኜት አንድ አመት ወይም ሶስት መቶ ስልሳ አምስት ቀን መሥራት ከነበረበት ዘንድሮ ይህ ቤተሰብ የአንድ አመት ቀለቡን ለማግኜት መሥራት ያለበት ሶስት ወይም አራት ወር ብቻ ከሆነ ነው። ይህን መሻሻል በምእራብ አገሮች እናየዋለን። በኢትዮጵያ ግን የለም።

በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ፲፰፻፷፪ (አስራ ስምንት መቶ ስልሳ ሁለት ዓ .ም .) አንድ የአሜሪካ ቤተሰብ የአንድ አመት ቀለቡን ለማግኜት ሁለት መቶ ሃያ አምስት ቀናት ይሠራ ነበረ። አሁን አንድ የኣሜሪካ ቤተሰብ የአመት ቀለቡን ለማግኜት የሚሠራው ሰላሳ ሶስት ቀን ብቻ ነው። በዚሁ በተመሳሳይ ጊዜ ኢትዮጵያን ብናይ ደግሞ ታሪኩ የተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኘዋለን። በ፲፰፻፷፪ (አስራ ስምንት መቶ ስልሳ ሁለት ዓ .ም .) ማረስ፣ መዝራት፣ መጎልጎል፣ ማጨድ፣ መከመር፣ ማበጠር፣ መፍጨት፣ መሽጥ እና ምግብ ማዘጋጀትን ጨምሮ፡ አንድ ቤተሰብ የአመት ቀለቡን ለማግኜት የሚያስፈልገው ዘጠና ቀን ብቻ መሥራት ነበረ። በዚህ ጊዜ አንድ ቤተሰብ ቢያንስ በሳምት አንድ ጊዜ ዶሮ፣ በወር አንድ ጊዜ ደግሞ ሙክት በግ አርዶ መብላት ይችል ነበር። ከምግቡም ጋር እርጎ ወይም አይብ፣ ወተት፣ ብርዝ፣ ጠጅ ወይም ጠላ ዘወትር ከቤት አይጠፋም ነበር። አሁን በስርቆት ሃብታም የሚሆኑትን ሳይጨምር አንድ የኢትዮጵያ ቤተሰብ አስር አመት እንኳን ቢሰራ በአስራ ስምንት መቶ ስልሳ ሁለት ዓ .ም . የነበረውን አይነት የአንድ አመት ቀለብ ማግኜት አይችልም።

እንግዲህ ከላይ እንዳየነው እድገት ማለት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ቤተሰቦች መልካም ኑሮ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ቀለብ ከአምና ዘንድሮ በቀላሉ ማግኜት ሲችሉ ነው። ታዲያ ይህ እድገት ከሆነ ግልባጩ ውድቀት ነውና የምእራባውያን የእድገት ዘመናት የኢትዮጵያውያን የውድቀት ሆነዋል ማለት ነው። በኢትዮጵያ ምን ቢቀየር ነው አንድ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ እንኳን ሊሻሻል የነበረውን ሳይቀር እያጣ የመጣው ?

የተቀየሩ ጉዳዮች

ከመቶ አመት በተለይም ከስልሳ አመት ወዲህ ባሉት አመታት ኢትዮጵያውያን ስለራሳቸው ጉዳይ እራሳቸው አያስቡም፤ የምእራባውያንን አስተሳሰብ ተውሰዋል፣ የራሳቸው የአለባበስ ባህል የላቸውም፤ የምእራባውያንን ልብስ ይለብሳሉ፣ እራሳቸው መሥራት አይችሉም፤ ምእራባውያን የሠሩትን ቁሳቁስ ይገበያሉ፣ ምእራባዉያን የሠሩትን መኪና ይነዳሉ፣ የራሳቸው ቋንቋ አይዳብርም፤ የምእራባውያንን ቋንቋ ይናገራሉ፣ የራሳቸው ባህል የላቸውም፣ የምእራባውያንን ባህል ባህላቸው አድርገዋል፣ የራሳቸው ጀግኖች የሏቸውም፤ ጀግኖቻቸው የምእራባውያን ጀግኖች ናቸው። ኑሮንም እንኖራለን ብለው መንገዳቸውን የሚቀይሱት ምእራባውያን አድርጉ ባሏቸው መንገድ ነው። ከዚህ ከስልሳ ዘመን ወዲህ የኢትዮጵያውያን ሙያ የምእራባውያን ቤት አዳሪነት ሆኖ ቆይቷል። ባጭሩ ኢትዮጵያ የምእራባውያን የአስተሳሰብ ቅኝ ግዛት ሆና በዚህ ዘመን የኖሩ አስተዳዳሪዎቿም ሆኑ የከተማው ሰዎች ከሁሉም በላይ የምእራባውያን አገልጋይ ለመሆንና በምእራባውያን ለመደመጥ፣ ከምእራባውያንም የፈቃድ ማህተም ለማግኜትና፥ ፍርፋሬያቸውንም ለመልቀም የሚሽቀዳደሙ፣ ስብእናቸውም የተዋረደ ሆነው ቆይተዋል። በምእራባውያን የተወጠኑት "ዘመናዊ የትምህርት ተቋማት" እየተባሉ የሚነገርላቸው ማሰልጠኛዎችም የኢትዮጵያውያንን አእምሮ ለምእራባውያን ትርፍና ቅኝ ገዢነት የሚያመቻቹ ተቋሞች ሆነው ሰንብተዋል። ለዚህም ነው የነዚህ ተቋማት ስልጡኖችም ሆኑ ሥራዎቻቸው ምእራባውያንን እንጂ ኢትዮጵያውያንን ሲጠቅሙም ሆነ ሲያገለግሉ የማናያቸው።

ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ጎዳዮች የኢትዮጵያውያን አዲስ አሠራሮች ከሆኑ በኋላ ከላይ እንዳየነው ኢትዮጵያውያን የለማኝነት ስም እስኪወጣላቸውና ዓለም በሙሉ እሲሳለቅባቸው ድረስ ረሃብተኛ ሆነዋል።

እራሳቸው ለራሳቸው ስለማያስቡ በዚህ ዘመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትርጉማቸውን የማያውቋቸውን ብዙ ፍልስፍናዎች ከምእራባውያን ተውሰው አሁንም ሃገራቸውን በማጥፋት ላይ ይገኛሉ። ሊበራል ዲሞክራሲ፣ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት፣ ነጻ ገበያ፣ ግሎባላይዜሽን ወዘተረፈ የሚባሉ ፌዘኛ አስተሳሰቦች በትውስት ከተገኙት ውስጥ አንዳንዶቹ ናቸው። ቀደም ሲል ማርክሲዝም ሌኒኒዝም የሚባል የውጭ አስተሳሰብ ምን እንደሆነ ሳያውቁ ተውሰው የኢትዮጵያ መመሪያ እናደርገዋልን ብለው ምን አይነት ውድቀት በኢትዮጵያ ላይ እንዳስከተሉ አይዘነጋም። አሁንም ብዙ ኢትዮጵያውያን "እኛ የምንነግራችሁን ፍልስፍና ተከተሉ" እያሉ፡ በምእራባውያን እየማሉ የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን እጣ ለውጭ አገር ተገዢነት የሚያደላድሉ አስተሳሰቦችን በኢትዮጵያ ሲያራግፉ እናያለን። እነዚህ ኢትዮጵያውያን ምእራባውያን ስለምን እንደሚናገሩ እንኳን ሳያውቁ "አሁን ዘመኑ የነጻ ገበያ ዘመን ስለሆነ ማንም ሰው ከውጭ አገር መጥቶ መሬት ተከራይቶ ያመረተውን ምርት ወደ ውጭ አገር ሊልክ ይችላል" እያሉ ኢትዮጵያን በመቸርቸር ላይ ይገኛሉ። እንደገናም ዘመኑ የሊበራል ዲሞክራሲ ነው እያሉ ምእራባውያን በደነገጉልን "የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት" መሠረት ኢትዮጵያ ልትከፋፈልና ልትቆራረጥ ትችላለች እያሉ እንዲሁ ኢትዮጵያውያንን ያለርስትና ያለዋስትና፣ ያለምግብም አስቀርተዋል፣ ለድህነትና ለዘላለም ተገዢነትም ዳርገዋል።

ምእራባውያንም እነዚህን የኢትዮጵያውያንን ውድቀት የሚያፋጥኑ ሰዎች ለማበረታታት ጉርሻ ይሰጣሉ። እነዚህ የምእራባዉያን አገልጋይ የሆኑ ኢትዮጵያውያንም ካገኙት ጉርሻ ትንሽ ቀንሰው ኢትዮጵያዊው በደሉን ችላ እንዲል ይደልሉታል። ኢትዮጵያዊው ከልጅ ልጅ የሚተላለፈውን ቅርሱን ተነጥቆ አንድ መንፈቅ የማይዘልቅ መደለያ ቢያገኝ ምን ይጠቅመዋል ?

የምእራባውያን "ኤኮኖሚክስ" በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያውያን ለራሳቸው ስንዴ፣ ዘንጋዳና ቡና ያመርታሉ እንበል። ወርቅም ያወጣሉ፣ ከብቶችም ያረባሉ፣ ንብ አርብተው ማር ይቆርጣሉ እንበል። ኢትዮጵያ ውስጥ ቡና ያለው ኢትዮጵያዊ ከፊሉን በስንዴ ለውጦ የእለት ምግቡን ሊያገኝ ይችላል። ከብት አርቢውም ከፊሉን በወርቅ ለውጦ ሊያጌጥ ይችላል። ምእራባውያንስ ቡናውን ወይም ማሩን ወይም ወርቁን ወይም የኢትዮጵያን የመልክአ ምድር አቀማመጥ እንደ መሣሪያ መጠቀም ሲፈልጉ ምን ያቀርባሉ ?

ምእራባውያን ያላቸው ወይ መኪና፣ ወይ ማዳበሪያ፣ ወይ ሲጋራ፣ ወይም ውስኪ ወይም፣ የጦር መሳሪያ ወዘተ ነው። ለምሳሌ መጀመሪያ ላይ አንድ ኩንታል ቡና ከኢትዮጵያ ለመውሰድ አንድ የቤት መኪና ይሰጣሉ እንበል። አንድ መኪና ሰጥተው አንድ ኩንታል ቡና እየወሰዱ መኖር ግን አይፈልጉም። ቢቻላቸው አንድ ሲጋራ ሰጥተው አንድ ኩንታል ቡና መውሰድን ይሻሉ። ይህን ለማድረግም ብዙ መላዎችን አዘጋጅተዋል። እነሱም ኢትዮጵያውያን የምእራቡን ነገር እንደሱስ የሚይዙበት መላዎች ናቸው። እነዚህንም መላዎች የሚራምደው አንዱ መንገድ ነጻ ገበያ የሚባለው ፈሊጥ ነው። ነጻ ገበያ ምእራባውያን የሚፈልጉትን ነገር እንደ ኢትዮጵያ ካሉ አገሮች በፈልጉት ዋጋና በሚፈልጉት ጊዜ የሚያገኙበት፤ ነገር ግን ኢትዮጵያውያንን በረሃብ ቸነፈር የሚገርፉበት አንዱ ስልት ነው። ነጻ ገበያ ነጻነቱ ለምእራባውያን ነው እንጂ ለኢትዮጵያዉያን አይደለም። በነጻ ገበያ ፍልስፍና ኢትዮጵያውያን እርስታቸውና ጥሬ ሃብታቸው የምእራባውያን ሲሆን በዚሁ በነጻ ገበያ ፍልስፍና መሠረት ኢትዮጵያውያን ከምእራባውያን የሚያገኙት አንድም የሚጠቅም ነገር አይኖርም።

ኢትዮጵያ በነጻ ገበያ ወጥመድ ከተጠመደች በዚህ በነጻ ገበያ አሰላለፍ ምእራባውያን የኢትዮጵያን ገነዝብ የመግዛት ችሎታ ባላቸው የረቀቁ ስልቶች እያዋረዱ ይሄዳሉ። ድሮ አንድ ኩንታል ቡና ሲወስዱ አንድ መኪና ሰጥተው ነበር እንበል። አሁን የኢትዮጵያ ገንዘብ ተዋርዷልና አንድ መኪና ከፈለጋችሁ መቶ ኩንታል ቡና ማቅረብ ይኖርባችኋል ይላሉ። አሁን ኢትዮጵያዊው ሁለት ምርጫ ያለው ይመስላል። አንደኛው መቶ ኩንታል ቡና ሰጥቶ አንድ መኪና መውሰድ ሲሆን ሁለተኛው መንገድ ደግሞ መኪናውን አልፈልግም ቡናውንም አልሰጥም ማለት ነው።

የመጀመሪያውን ምርጫ ምእራባውያን ያቀዱት ስለሆነ ለምእራባውያን ተስማሚ ነው፤ ኢትዮጵያዊውን ግን ረሃብተኛ ያደርገዋል። ኢትዮጵያዊው ረሃብተኛ መሆንን ስለማይፈልግ ቡናውን አልሰጥም መኪናውም ይቅርብኝ አለ እንበል። ምእራባውያን ለዚህ ጊዜ ያዘጋጇቸውን መላዎች ይጀምራሉ። በአንዱ የኢትዮጵያ ሠፈር ይሄዱና አንዱን ኢትዮጵያዊ "ያንተ ዘመዶች በዛኛው ሠፈር በሚኖረው ኢትዮጵያዊ የተጨቆኑ ናቸው፤ ከዚህ ከጭቆና ነጻ ለመውጣት ብትሻ እኛ እንረዳሃለን" ብለው መሣሪያ ያስታጥቁና ጦርነት ያስጀምሩታል። ያ ቡናየን አልሰጥም መኪናም አልፈልግም ያለው ኢትዮጵያዊ የውጭ አገር ጦር መሣሪያ ይዞ ሊወጋው የመጣውን ወንድሙን የሚከላከልበት መሣሪያ የለውም። በዚህ ጊዜ ወደ ምእራባውያን ይሄድና እባካችሁን የምዋጋበት መሣሪያ ስጡኝ ይላቸዋል። እነሱም ቡናውን አምጣና መሣሪያ እንሰጥሃልን ይሉታል። አሁን የሚፈልገውን ቡና ሰጥቶ ከመጀመሪያው ያላቀደውንና ወደ ምግብነት ሊቀይረው የማይችለውን ሰው የመግደያ መሣሪያ ይገበያል። በዚህ ጊዜ መኪናውን ቢፈልግ አንድ ሺህ ኩንታል ቡና አምጣና መኪናውን ታገኛለህ ይሉታል። እነሆ እንግዲህ እስካሁን የቆየው የኢትዮጵያና የምእራባውያን ግንኙነት አጭር ታሪክ ይህ ነው። ኢትዮጵያዊው በዚህ በምእራባውያን ምርጫ ስለተጓዘ ኑሮው ባለፉት አንድ መቶ አመታት እንደቆረቆዘ እናያለን። ኢትዮጵያዊው የምእራባውያንን ቀንበር ሁልጊዜ እንደተሸከመ እንዲኖርም ብዙ ወጥመዶች ተጠምደውበታልና አሁን በያዘው መንገድ ቢቀጥል ቀንበር በፍጹም ከላዩ ላይ ሊወርድ አይችልም።

የወደፊቷ ኢትዮጵያ ግን መሪዋ እግዚአብሔር ነውና ምእራባውያን ባዘጋጁላት ወጥመድ እራሳቸው እንዲጠመዱ የሚያደርግ ጥበብ ይኖራታል። በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ሰጪ እንጂቀባይ አይሆኑም። ጥበብም ከኢትዮጵያ ይፈልቃል እንጂ ኢትዮጵያ የምእራባውያን የፍልስፍና ፍርፋሪ ለቃሚ አትሆንም። የፈረንጅ ፍልስፍናን ለማራመድ ሲባል ኢትዮጵያውያን ዘላቂ እርስታቸውን አሳልፈው የሚሰጡ፣ ልጆቻቸውንም ያለ ርስትና ያለ መስሪያ ቦታ የሚያስቀሩ ቂሎች አይሆኑም።

በወደፊቷ ኢትዮጵያ የሰው ፍልስፍና በኢትዮጵያ ላይ አይሰለጥንም። የኢትዮጵያ ፈላስፋዋ ፈጠሪዋ እግዚአብሔር ነውና። በኢትዮጵያ የሚደረግ ማንኛውም የሰው እንቅስቃሴ ቋሚ መለኪያ ወይም መመዘኛ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው። ምእራባውያን እራሳቸውን ለመጥቀም ነጻ ገበያ የሚባል ፍልስፍና እነሆ አመጣንላችሁ ቢሉ ኢትዮጵያውያን መልሰው "ይህ ለኢትዮጵያዊው ምኑ ነው ?" ይላሉ። "ኤኮኖሚክስ" የሚባለው የፈረንጅ ትምህርት ለአንድ ኢትዮጵያዊ የማይገባው ከሆነ ለኢትዮጵያ ምን ጥቅም አለው ? ሰው ባልገባው ፍልስፍና ውስጥስ ለምን ይነከራል ? ምእራባውያን በዚህ ፍልስፍናቸው እጅግ የተራቀቁ ከሆነ ትምህርቱን ከምእራባዉያን ተማርን የሚሉ ኢትዮጵያውያን ከምእራባውያን ጋር በዚህ ምእራባውያን በተራቀቁበት ቋንቛ ማውጋታቸው ሞኝነት አይሆንም ወይ ? ምክንያቱም የምእራባውያን "ነጻ ገበያ" ፍልስፍና የመወዳደር ወይም የመፎካከር እንጂ የመረዳዳት አይደለምና። ታዲያ ከፈረንጅ ያነሰ እውቀት ያላቸው ኢትዮያውያን በአሰልጣኞቻቸው ላይ ሊሰለጥኑ ይችላሉን ? ስለዚህም የአሰልጣኞቻቸውን ትምህርት ከሚያራምዱ ሰዎች ለኢትዮጵያ የሚገኝ ጥቅም አይኖርምና በውጭ ፍልስፍና የተማረኩ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን የህብረምጣኔ መንገድ አይቀይሱም። ኢትዮጵያ ጥቅም የምታገኘው ሰዎቿ አናውቅም ብለው ሲጀምሩ ነው።

"አላውቅም"፥ የወደፊቷ ኢትዮጵያ የንግድ ቋንቋ።

ምእራባውያን በብዙ መንገድ ወደአፍሪካ እና ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል። ከመጡባቸው ብዙ መንገዶች ውስጥ አንድም የቅንነት መንገድ ኖሮ አያውቅም። ምእራባውያን ወደ አፍሪካ የሚመጡት ወይ የሚነጥቁት መሬት ፍለጋ፣ ወይም ቅኝ ለመግዛት፣ ወይም አፍሪካውያንን ለማዋጋት፣ ወይም የኑክሌር አተላ ለመድፋት፣ ወይም በሺታ ለማራገፍ፣ ወይም የዱር እንስሳትን፣ እጸዋትን እና አትልክቶችን ወደአገራቸው ለመውሰድ፣ ወይም አፍሪካውያንን ለመሳለቂያ በቪዲዮ ለመቅረጽ ወይም በጋዜጣ ለመስደብና ለመሳሰሉት ጉዳዮች ነው። ባጭር አነጋገር የአፍሪካ ሰዎች ምእራባውያን የሚታመን ወይም ቅንነት ያለበት ሥራ ሲሰሩ አይተው አያውቁም። ታዲያ ሰው ጅል ካልሆነ በቀር ከማያምነው ሰው ምክርን ይሻልን ?

ስለዚህም ጉዳይ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ሰውን ሁሉ ትወዳለች፤ ነገር ግን አንድም የሰው ፍልስፍና በፊቷ ተአማኒነት አይኖረውም። ከምእራባውያንም ሆነ ከአረቦች፣ ካፋርሶች፣ ከቻይኖች ወይም ከህንዶች ጋር የሚኖራት ግንኙነት መጀመሪያ ፍልስፍናቸውን ካለማመን ይጀምራል። እነዚህ የውጭ አገር ሰዎች "ነጻ" ገበያ ቢሏት ኢትዮጵያ መልሷ ነጻ ገበያ ምን እንደሆነ እኔ አላውቅም ይሆናል። ቀጥላም … ይልቁንስ በማውቀውና በሚገባኝ መንገድ አስረዱኝ ትላቸዋለች። ይህ እናንተ ያመጣችሁት ሸቀጥ የኢትዮጵያውያንን ኑሮ እንዴት እንደሚያሻሽል አስረዱኝ ትላቸዋለች። መሻሻል ማለት ደግሞ እነሱ የሚያቀርቡት ትርጉም ሳይሆን ኢትዮጵያውያን እራሳቸው መሻሻል ማለት ይህ ነው ብለው የደነገጉት ትርጉም ይሆናል። ከሁሉም በፊት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፣ ከአረጋዊ እስከ ህጻን፥ አንድም ሳይቀር በየቀኑ ደስ የሚያሰኘውን ምግብ የሚበላ፣ የሚጠጣው ንጹህ መጠጥ በየቀኑ የሚያገኝ፣ ልብሱ እና ቤቱ ሁል ጊዜ ንጹህ የሆነ፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ የሚያድርበት ቤት ያለው፤ በቤቱም ውስጥ ብርድ ወይም ተባይ የማያገኘው፣ የማይጎሳቆል ይሆናል። ከውጭ ጋር የሚደረግ ምንም አይነት ንግድ ከዚህ ከኢትዮጵያ አኗኗር የሚያጎድል ከሆነ አፍራሽ ንግድ ነው። የኢትዮጵያውያን የወደፊት አኗኗር መሠረቱ ይህ ነው።


በምድርና በሰማይ የምናያቸውን እጹብ ድንቅ ትእይንቶች የፈጠረ አምላክ ኢትዮጵያን በቸርነቱ ይጎብኛት።


ሙሉጌታ። ካሊፎርኒያ። ጥቅምት ፳ ቀን ፪፲፻፬ ዓ . ም .





የወደፊቷ ኢትዮጵያ ህብረምጣኔ።

 HOME